የአርበኞች ግንቦት 7 ንቅናቄ 17 እስረኞችን አስለቀቀ

(ኢሳት ዲሲ–ጥር 29/2010)

 

የአርበኞች ግንቦት 7 ንቅናቄ በሰሜን ጎንደር ዞን ጎንደር ዙሪያ ወረዳ ማክሰኚት ከተማ በሚገኘው እስር ቤት ላይ ባደረሰው ጥቃት 17 እስረኞችን ማስለቀቁን ለኢሳት በላከው መግለጫ አስታወቀ።

አርበኞች ግንቦት 7 ንቅናቄ መገለጫ እንደሚያመልከተው ዘመቻ ነጻ ትውልድ በሚል መጠሪያ ማክሰኝት እስር ቤት ላይ በተፈጸመጥቃት ነው 17 እስረኞች ነጻ የወጡት።

ትላንት ለሌት በኢትዮጵያ ሰአት አቆጣጠር 9 ሰአት ላይ ፈጸምኩት ባለው በዚሁ ጥቃት የእስር ቤቱ ተረኛ መኮንንና ጠባቂ ፖሊስ ተገድለዋል ብሏል።

ሌሎች ሶስት ፖሊሶች መቁሰላቸውንም አስታውቋል።

ማክሰኚት በሚገኘው እስር ቤት በፖለቲካ አመለካከታቸው የታሰሩትን ጨምሮ ከ160 በላይ ወጣቶች ስቃይና ድብደባ እየተፈጸመባቸው እንደሚገኙ መግለጫው ጠቅሷል።

እስር ቤቱ ከፍተኛ ሰቆቃ የሚካሄድበት በመሆኑ ለጥቃት እንዲመረጥ እንዳደረገው ገልጿል።

የአካባቢው ነዋሪዎች እንደሚሉት ከእስር ቤቱ የሚሰማው የስቃይና የጣር ድምጽ እረፍት የሚነሳ ነው።

በየጊዜውም የተኩስ ድምጽ እንደሚሰሙ የገለጹት ነዋሪዎች የአማራ ወጣቶችን በምርመራ በማሰቃየት የሚታወቅ እስር ቤት ነው ማለታቸውን የደረሰን መረጃ ያመለክታል።

የአርበኞች ግንቦት ሰባት ንቅናቄ ፈጸምኩት ያለውን ጥቃት በተመለከተ ከሌላ ወገን ለማረጋገጥ ያደረግነው ጥረት አልተሳካም።

የአማራ ክልል መንግስትም ጥቃቱን በተመለከተ ያለው ነገር የለም።

ከዚሁ ጋር በተያያዘ ከአንድ ሳምንት በፊት በመተማ ዮሃንስ ለተፈጸመው የቦምብ ጥቃት የአርበኞች ግንቦት ሰባት ንቅናቄ ተጠያቂ መሆኑን የምዕራብ ጎንደር ፖሊስ መምሪያ አስታውቋል።

የአማራ ክልል ቴሌቪዥን ላይ ቀርበው የተናገሩት የምዕራብ ጎንደር ፖሊስ መምሪያ ዋና ኢንስፔክተር እንደገለጹት ታጣቂዎቹ በከተማው አስተዳደር ሕንጻ ላይ በፈጸሙት ጥቃት ዘጠኝ ሰዎች ላይ ጉዳት አድርሰዋል።

አርበኞች ግንቦት 7 በወቅቱ ጥቃት መፈጸሙንና በከተማዋ የፍትህና ጸጥታ አመራሮች ላይ ሳይቀር ጉዳት ማድረሱን መግለጹ ይታወሳል።

በሌላ በኩል በላሊበላ ከተማ ውጥረት መንገሱን የደረሰን መረጃ አመልክቷል።

ሕገወጥ ቤት እናፈርሳለን በሚል የተንቀሳቀሰው ግብረ ሃይል ከነዋሪዎች ጋር የተጋጨ ሲሆን ጉዳት መድረሱም ታውቋል።

የአጋዚ ወታደሮች ወደ ከተማዋ በመግባት ሁኔታውን ለመቆጣጠር ጥረት እያደረጉ ቢሆንም ሕዝቡ የአጋዚ ጦር መግባቱን በመቃወም ላይ መሆኑን የደረሰን መረጃ ያመልከታል።