(ኢሳት ዲሲ–ጥር 28/2010)
በፈረንሳይ ፓሪስ ለ130 ሰዎች ዕልቂት ምክንያት በሆነው የሽብር ድርጊት ተሳታፊ የነበረው ተጠርጣሪ ለመጀመሪያ ጊዜ ፍርድ ቤት ቀረበ።
ለዳኞቹ ምንም የምላችሁ ነገር የለም ዝምታዬ ለኔ የመከላከያ ማስረጃዬ ነው ማለቱም ተመልክቷል።
እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር ህዳር 13/2015 በፈረንሳይ ፓሪስ የሙዚቃ ዝግጅት በሚካሄድበት አዳራሽ፣በስታዲየምና በሆቴል ላይ በተሰነዘረው ተከታታይ የሽብር ጥቃት ለ130 ሰዎች ማለቅና በመቶዎች ለሚቆጠሩ መቁሰል ተጠያቂ ከነበሩት ተጠርጣሪ አሸባሪዎች አንዱ የሆነው የ28 አመቱ ሳላህ አብዱሰላም በቁጥጥር ስር የዋለው ከወራት በኋላ በቤልጂየም መዲና ብራስልስ እንደሆነ መረጃዎች ያመለክታሉ።
ፖሊሶች በደረሳቸው ጥቆማ መሰረት ሊይዙት በአሰሳ ላይ በነበሩበት ወቅት በፖሊሶች ላይ ተኩስ በመክፈት በፈጸመው ወንጀል በቤልጂየም መዲና ብራስልስ ዛሬ ፍርድ ቤት ቀርቧል።
በፈረንሳይ ውስጥ ለፈጸመው የሽብር ድርጊት ወደ ፓሪስ ተልኮ ለፍርድ እንደሚቀርብም ይጠበቃል።
እስከተያዘው የፈረንጆቹ አመት ማብቂያም በብራስልስ እንደሚቆይም ተገልጿል።
በቀረበበት በአሁኑ ወንጀል ጥፋተኛ ሆኖ ከተገኘም እስከ 40 አመት እስራት እንደሚጠብቀው ከቢቢሲ ዘገባ መረዳት ተችሏል።
በምርመራ ወቅት ለፖሊሶች ቃሉን ለመስጠት ፈቃደኛ ያልሆነው ሳላህ አብዱሰላም ፍርድ ቤት በቀረበበትም ወቅት ዝምታን መርጧል።
ሆኖም በዳኞቹ ለቀረቡለት ጥያቄዎች ምላሽ ባይሰጥም “ዝምታዬ ወንጀለኛ አያደርገኝም፣ዝምታዬ መከላከያዬ ነው”ከማለቱም ባሻገር “እናንተንም ሆነ የእናንተን ተባባሪዎች አልፈራም”ሲል በችሎቱ ውስጥ ተደምጧል።
ሳላህ አብዱሰላም እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር በህዳር 2015 በፓሪስ በተፈጸመው የሽብር ጥቃት ከአሸባሪዎቹ አንዱ የነበረው ወንድሙ ብራሃም አብዱሰላም በአጥፍቶ መጥፋት ሕይወቱ ያለፈ መሆኑ ይታወሳል።
ከወራት በኋላ ብራስልስ ውስጥ ተያዘ እንጂ ከተጠርጣሪዎቹ ውስጥ ያመለጠው ብቸኛው ሳላህ አብዱሰላም ነበር።
በአውሮፓ ውስጥ እጅግ ተፈላጊ ወንጀለኛ በሚል ሲታደን ቆይቶ ከወራት በኋላ የተያዘውና ዛሬ ፍርድ ቤት የቀረበው የ28 አመቱ ሳላህ አብዱሰላም ከሞሮኳዊ ቤተሰብ ቤልጂየም ውስጥ የተወለደ ሲሆን በዜግነት ደግሞ ፈረንሳዊ ነው።