(ኢሳት ዲሲ–ጥር 28/2010)
የኢትዮጵያው አገዛዝ በሚቆጣጠረው ኢትዮ ሳት ሳተላይት የግልም ሆነ የመንግስት ቴሌቪዥን ጣቢያዎች በግዳጅ እንዲሰራጩ በብሮድካስት ባለስልጣን የቀረበው ሃሳብ ተቀባይነት ማጣቱ ተገለጸ።
በተለይ የኦሮሚያና የአማራ መገናኛ ብዙሃን በዚህ ሳተላይት በኩል እንዲሰራጩ የተደረገው ሙከራ ክልሎቹ ፈቃደኛ ባለመሆናቸው ሊሳካ አልቻለም።
“ኢትዮ ሳት” በኢንሳ በኩል ቁጥጥር የሚደረግበትና ከፈረንሳይ ኩባንያ አገዛዙ በውድ ዋጋ የተከራየው ሳተላይት ነው።
በሳተላይቱ ከ35 በላይ ቻናሎች ሊሰራጩበት እንደሚችልም ነው የተነገረው።
በኢትዮ ሳት በኩል የግልም ሆነ የአገዛዙ የሳተላይት ቴሌቪዥን ጣቢያዎች እንዲያስተላልፉ የተፈለገውም በስርጭቱ ላይ ቁጥጥር ለማድረግ እንደሆነ ታዉቋል።
የኢትዮጵያ ሳተላይት ቴሌቪዥንና ሬዲዮ/ኢሳት/ ከአየር ላይ እንዲወርድ አገዛዙ ከፈረንሳዩ ኩባንያ ጋር በመደራደር “ኢትዮ ሳት” በሚል የሳተላይት ኪራይ ግዥ መፈጸሙም የሚዘነጋ አይደለም።
እናም “በኢትዮ ሳት” ሳተላይት ዝግጅቶቻቸውን እንዲያሰራጩ የተጠየቁት የኦሮሚያና የአማራ ክልል መገናኛ ብዙሃን ድርጅቶች ነጻነታችንን ይጋፋል በሚል ፈቃደኛ አለመሆናቸው ነው የተነገረው።
ቁም ነገር መጽሔት የብሮድካስት ባለስልጣን የኮሚኒኬሽን ዳይሬክተር የሆኑትን አቶ ገብረጊዮርጊስ አብርሃን ጠቅሶ እንደዘገበው የቴሌቪዥን ጣቢያዎቹ “በኢትዮ ሳት” በግድ እንዲያሰራጩ የተፈለገው የውጭ ምንዛሬን ለማስቀረት ነው።
የቴሌቪዥን ጣቢያዎቹ በውጭ ምንዛሪ እየከፈሉ ከሌላ ሀገር ሳተላይት ጋር ከሚሰሩ በብር ከፍለው በሀገሪቱ ያለውን የውጭ ምንዛሪ እጥረት መከላከል የግድ ነው ብለዋል።
የኦሮሚያና የአማራ ክልል መገናኛ ብዙሃን ድርጅቶች ለምን እንገደዳለን፣አንፈልግም ማለታቸውን ተጠይቀውም የአየር ሞገዱ የሚተዳደረው በፌደራል ስለሆነ ይህን ውስን ሃብት መጠቀም ግዴታችን ነው ብለዋል።
የአማራና የኦሮሚያ ቴሌቪዥኖች ግን መቆጣጠሪያውን ወይንም ሪሞት ኮንቶሮሉን ለኢንሳ በማስረከብ ነጻነታችንን አሳልፈን አንሰጥም በሚል በእምቢተኝነታቸው ጸንተዋል።