(ኢሳት ዲሲ–ጥር 21/2010)
የወልዲያው ተቃውሞ ዳግም ተቀሰቀሰ።
መሀል ወልዲያ ዛሬ ጠዋት ከፍተኛ የህዝብ ተቃውሞ ሲደረግና የመንግስት ተቋማት ላይ ጥቃት ሲሰነዘር እንደነበርም ለማወቅ ተችሏል።
ከቀትር በኋላ በቤት ውስጥ የመቀመጥ የስራ ማቆም አድማ የተመታ ሲሆን ወልዲያ ሁሉ ነገር ከእንቅስቃሴ ውጭ ሆኖ እንደዋለም ታዉቋል።
ህዝባዊ አመጹ በተለያዩ ከተሞች እየተካሄደ ነው።
የመርሳ ከተማ አስተዳዳሪ መገደላቸውም ታውቋል።
በሲሪንቃ በርካታ ተሽከርካሪዎች ተቃጥለዋል። መንገዶች ተዘግተዋል። የትራንስፖርት አገልግሎት ተቋርጧል።
የመርሳው ተቃውሞ ለሶስተኛ ቀን መቀጠሉም ይነገራል።
የሰሜን ወሎ ዋና ዋና መንገዶች በሙሉ ከአገልግሎት ውጪ መሆናቸውን የደረሰን መረጃ ያመለክታል።
ህዝቡ በጥምቀት በዓል የተገደሉትን ለመዘከር የሻማ ማብራት ስነስርዓት ላይ ነበር በወልዲያ አዳጎ አካባቢ።
ድንገት የመከላከያና የአጋዚ ሃይል አካባቢውን ወረረና ነገሮች ተቀያየሩ።
በተኩስ እሩምታ፣ በድብደባና ሩጫ አዳጎ ሰላማዊ አየሯ በቅጽበት ደፈረሰ።
ጠዋት ይህ በሆነ ከሰዓታት በኋላ መሃል ወልዲያ ፒያሳ የህዝብ አመጽ ፈነዳ።
የተገኘ የመንግስት ተቋም ላይ ርምጃ ተወሰደ። ከስርዓቱ ጋር ግንኙነት ያላቸው ግለሰቦች ንብረት ላይም ጥቃት ተሰነዘረ።
አሁንም የህወሃት አገዛዝ ታጣቂዎች፣ የመከላከያና የአጋዚ ሰራዊት አባላት በበርካታ ወታደራዊ ተሽከርካሪዎች ተጭነው መሃል ወልዲያ ላይ ሰፈሩ።
ያገኙትንም መደብደብ ጀመሩ። አንድ የኢሳት እማኝ ከወልዲያ እንደገለጸው የአጋዚ ሰራዊት የወሰደው የጭካኔ ርምጃ ቃል የሚገልጸው አይደለም።
መጀመሪያ ላይ በአስለቃሽ ጭስ ለመበተን የሞከረው የህወሀት ሃይል ህዝቡ ሲጠነክርበት ተኩስ መጀመሩን ነው ከደረሰን መረጃ ለማወቅ የተቻለው።
ህዝቡ በቁጣ በወሰደው ርምጃ የቀበሌ ጽህፈት ቤት አቃጥሏል። ከአገዛዙ ጋር ግንኙነት ያላቸው ግለሰቦች ንብረት ላይ ጥቃት ሰንዝሯል።
ከቀትር በኋላ በወልዲያ የነበረው ሁኔታ ሁለም ነገር ቀጥ ያለ ነበር።
መስሪያ ቤቶች፣ የንግድ ቦታዎች፣ ትምህርት ቤቶች በሙሉ ተዘግተው የዋሉ ሲሆን በቤት ውስጥ የመቀመጥ አድማ መመታቱም ታውቋል።
የወልዲያ ህዝብ ከአቶ ገዱ አንዳርጋቸው በቀር የትኛውም የብአዴን አመራር እንዳይመጣ ሲል ማስጠንቀቁንም ለማወቅ ተችሏል።
በሌላ በጎብዬ ህዝብን ለመሰብሰብ የሞከረው የፌደሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አቶ ያለው አባተ ከህዝቡ ጥቃት ሊፈጸምበት እንደነበረ የገለጹ የኢሳት ምንጮች በከተማዋ ሽማግሌዎች እርዳታ ተርፎ ከከተማ እንዲወጣ መደረጉን ጠቅሰዋል።
በተያያዘ ዜናም ባለፈው ቅዳሜ በመርሳ የተጀመረው ህዝባዊ ተቃውሞ ዛሬ በተለያዩ የከተማዋ አካባቢዎች ቀጥሏል።
ከ13 ሰዎች በላይ የተገደሉባት መርሳ የህወሃት አገዛዝ ከፍተኛ የሰራዊት ሃይል በማከማቸት ህዝቡ ላይ የግፍ ርምጃ መፈጸሙን እንደቀጠለ የሚያሳዩ መረጃዎች እየወጡ ነው።
በትላንትናው ዕለት የመርሳ ከተማ አስተዳዳሪ ተገድለዋል። በሲሪንቃ ትላንት ከፍተኛ የህዝብ ተቃውሞ ተከስቷል።
የአገዛዙ ደጋፊ ሚዲያዎችም የትላንቱን የሲሪንቃ አመጽ በስፋት ዘግበዋል። በሲሪንቃ በርካታ ተሽከርካሪዎች ተቃጥለዋል። መንገዶችም ተዘግተዋል፡፡
የትራንስፖርት አገልግሎትና የንግድ እንቅስቃሴዎች ተቋርጠዋል።
በመርሳ ከተማ ፍርድ ቤቶች፣ ሆቴሎችና ሱቆች እንደተቃጠሉና ለቁጥር የሚያዳግቱ የንግድ ቤቶችና የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች መቃጠላቸውን ሪፖርተር ጋዜጣ ዘግቧል።
በመርሳ ወታደሮች ተሰብስበው በነበረበት ወቅት በተወረወረ ፈንጅ 18 ወታደሮች ጉዳት እንደደረሰባቸው መረጃዎች አመልክተዋል።
16 ወታደሮች ህክምና አግኝተው ከሆስፒታል ሲወጡ፣ ሁለት ወታደሮች ግን በጽኑ ቆስለው ወልድያ ልዩ ክትትል በሚደረግበት ክፍል ውስጥ ተኝተዋል።
በሰሜን ወሎ ውጥረቱ ተባብሷል። ደሴ፣ ኮምቦልቻና ሀይቅ ተጨማሪ የአጋዚ ወታደሮች እንዲሰማሩ ተደርጓል።