(ኢሳት ዲሲ–ጥር 18/2010)
ከማረሚያ ቤት ለሚለቀቁ ታሳሪዎች የመጓጓዣና ሌሎች ወጪዎች የተመደበውን 78 ሺ ያህል ብር የቂሊንጦ ማረሚያ ቤት ሀላፊዎች እንደተከፋፈሉት ከማረሚያ ቤት የተገኘው መረጃ አመለከተ።
በፌደራል ደረጃ ይፈታሉ ተብሎ ስማቸው ከተዘረዘረው 115 እስረኞች ውስጥ አሁንም ማረሚያ ቤት የሚገኙት ታሳሪዎች ቁጥር ስድስት መድረሱ ታውቋል።
ከሳምንታት በፊት ክሳቸው ተቋርጦ ይለቀቃሉ ከተባሉት የፌደራል እስረኞች መካከል 115 ያህሉ ተለቀዋል ቢባልም የተወሰኑት እስካሁን በእስር ላይ እንደሚገኙ ለማወቅ ተችሏል።
በሳምንቱ የኢሳት ዘገባችን ተፍትተዋል ከተባሉት ማካከል 4 ያህሉ አምስት ዓመትና ከዛ በላይ በሆነ ጊዜ እንደተፈርደባቸው ገልጸናል ።
ዛሬ የወጡ መረጃዎች እንደሚያሳዩት ደግሞ የተፈረደባቸውን ጨምሮ ስድስት የሚሆኑት ቃሊቲ ማረሚያ ቤት እንደሚገኙ ለማወቅ ተችሏል።
ሉሉ መሰለ፣ በጋሻው ዱንጋ፣ ጌታሁን ቀጶና መርደኪዮስ ሽብሩ የተፈረደባቸው ሲሆኑ ከነዚህ ሌላ ያረጋል ሙሉዓለም፣ዲንሳ ፋፋ እና ቶሎሳ በዳዳ በቃሊቲ እስርቤት እንደሚገኙ ለማወቅ ተችሏል።
በሌላ በኩል ለእነዚህ ተፈተዋል ለተባሉትና ስማቸው ለተዘረዘሩት 115 እስረኞች የተለያየ ወጪ የተመደበውን ገንዘብ የቂሊንጦ ማረሚያ ቤት ሃላፊዎች እንደተከፋፈሉት ታውቋል።
ከማረሚያ ቤት የተገኘው መረጃ እንደሚያሳየው በታሳሪዎቹ ስም ለተለያዩ ዝግጅቶች በሚል ለእያንዳንዳቸው 695 ብር ወጪ እንዲሆን ትእዛዝ ተላልፎ ነበር።
የማረሚያ ቤት ማህተም ያላረፈበት ይህ መረጃ ለታሳሪዎቹ ለመጓጓዣ፣ለቡና፣ለፈንዲሻ፣ ለሰንደልና ለእጣን በሚል በጀት ተሰርቶለታል።
ይህም ገንዘብ አቶ ቴድሮስ አብቹ በሚባሉ ግለሰብ ስም ወጪ እንዲሆን ትእዛዝ ተሰቷል።
ይህ በታሳሪዎቹ ስም ወጪ የተደረገው ገንዘብ ከእስር የተለቀቁት እንዳልደረሳቸውና የቃሊቲ እስር ቤት ሀላፊዎች በአንድ እስረኛ ስም የተመደበውን 695 ብር በአጠቃላይ 77 ሺ 925 ብር ተከፋፈለውታል መባሉን ለማወቅ ተችሏል።
በሕወሀት የሚመራው አገዛዝ በሀገሪቱ የተከሰተውን ህዝባዊ እምቢተኝነት መቆጣጠር እንዳልቻለ ታውቋል።
በተለያዩ አካባቢዎች የተነሳበትን ታቃውሞ ለማክሸፍና የአለም አቀፍ ሀገራትና ተቋማትን ትኩረት ለመሳብ የፖለቲካ እስረኞችን እፈታለሁ ያለው ህወሃት የተናገረውና እየተገበረ ያለው እውነታ ግን እርስ በርሱ የሚጋጭ መሆኑን በተለያዩ ዘገባዎቻችን ማሳየታችን ይታወሳል።