(ኢሳት ዲሲ–ጥር 18/2010)
ነባር አመራሮችን ጨምሮ የድርጅቱን ሕልውና እየገመገመ ያለው የብአዴን ማዕከላዊ ኮሚቴ ስብሰባ በተንጠባጠበ ሁኔታ ሲካሄድ ቆይቶ መቋረጡ ታወቀ።
በማዕከላዊ ኮሚቴ ስብሰባው 22 አባላት ሕወሃት ባስቀመጠላቸው አቅጣጫ መሰረት በጥልቅ ተሃድሶው አፈጻጸም ላይ ውይይት ቢጀምሩም በወልዲያና በቆቦ የተፈጸመው ጅምላ ግድያ በመካከላቸው መከፋፈልን ፈጥሯል።
የብአዴን ማዕከላዊ ኮሚቴ በአቶ አዲሱ ለገሰና በአቶ በረከት ስምኦን አቅጣጫ ሰጭነት ለክልልና ለተወካዮች ምክር ቤት የማሟያ ምርጫ በሚተኩ አባላት ዙሪያም ይመክራል ተብሏል።
የወልዲያውን ጅምላ ጭፍጨፋ ተከትሎ በሰሜን ወሎ ዞን ቆቦ የቀጠለው ሕዝባዊ አመጽ የብአዴን ማዕከላዊ ኮሚቴ አባላት በተረጋጋ ሁኔታ ስብሰባቸውን እንዳያካሂዱ አድርጓቸዋል።
የማዕከላዊ ኮሚቴ ስብሰባውን አቋርጠው ወደ ቆቦ ያመሩት የአማራ ክልል ፕሬዝዳንት አቶ ገዱ አንዳርጋቸው የሰው ሕይወት መጥፋቱ አሳዝኖኛል ብለዋል።
የብአዴን ነባር አመራር ሆነው ፓርቲውን እያሽከረከሩ ያሉት አቶ አዲሱ ለገሰና አቶ በረከት ስምኦን ሲሆኑ በቡድንና በአንጃ የተከፈሉት የማዕከላዊ ኮሚቴ አባላት በወልድያውና በቆቦው ግጭት ሳቢያ መከፋፈላቸው ተነግሯል።
የውዝግባቸው መንስኤ ደግሞ ግጭቱን በክልሉ የጸጥታ ሃይል መቆጣጠር ይሻላል?ወይንስ የመከላከያ ጣልቃ ገብነት አስፈላጊ ነው የሚለው ጉዳይ መሆኑን የኢሳት ምንጮች ገልጸዋል።
በእነ አቶ ገዱ የሚመራው የብአዴን ቡድን በአማራ ክልል የጸጥታ መዋቅር ግጭቱን መከላከል ይቻላል የሚል እምነት አለው።
እነ አቶ አለምነው ያሉበትና የሕወሃት ተላላኪ ነው የሚባለው ቡድን ግን መከላከያ ካልገባ በሕወሃት አባላት ላይ የሚፈጸመውን ግድያ ማስቆም አይቻልም የሚል ክርክር አቅርቧል።
እናም አቶ ገዱ የመከላከያን ጣልቃ መግባት የሚፈልጉትን የብአዴን አመራር አባላት ለችግሩ ተጠያቂ ናቸው ማለታቸውን ምንጮቹ ገልጸዋል።
በባህር ዳር ከተማ ተጀምሮ የተቋረጠው የብአዴን ማዕከላዊ ኮሚቴ ስብሰባ የቴዲ አፍሮ ኮንሰርት አፈጻጸምን ከሂደቱ እስከ ፍጻሜው በነበረው ሁኔታ ላይ መረጃ እንደቀረበለትም ለማወቅ ተችሏል።
የብአዴን ማዕከላዊ ኮሚቴ አባላት በድንገተኛ አጋጠሚዎችና አስገዳጅ ሁኔታዎች ስብሰባ ቢያቋርጡም ውይይቱን ለመቀጠል ከ4 ቀናት በኋላ እንደገና እንደሚመለሱ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።
በማዕከላዊ ኮሚቴው ስብሰባ የቀበሌና የአካባቢ ምርጫ ስለሚካሄድበት እንዲሁም ለክልልና ለተወካዮች ምክር ቤት የማሟያ ምርጫ በሚተኩ አባላት ዙሪያም የመክርበታል ተብሏል።
በዚሁም ለፌደራልና ለክልል ከፍተኛ የስልጣን ቦታዎች የሚታጩ አዳዲስ ሰዎች በዚሁ መሰረት ሽግሽግ እንደሚያደርግ ነው የተነገረው።
በዚሁም መሰረት አቶ ገዱ አንዳርጋቸውን ከስልጣን ለማንሳትና ሌላ ሰው ለመተካት ዝግጅት እየተደረገ መሆኑ ታውቋል።