(ኢሳት ዲሲ–ጥር 18/2010)
በወልዲያና በቆቦ በኢትዮጵያውያን ላይ የቀጠለውን ግድያ በማውገዝ የሃይማኖት ተቋማት መግለጫ አወጡ።
በስደት የሚገኘው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ በየአብያተክርስቲያናቱ ለሟቾች ጸሎተ ፍትሃት እንዲደረግ ወስኗል።
ለመከላከያ ሰራዊቱም ጥሪ አቅርቧል።
የኢትዮጵያ ሙስሊሞች ንቅናቄ ሕብረት በበኩሉ ባወጣው መግለጫ የወሎ ሕዝብ እየከፈለ ላለው መሽዋዕትነት አክብሮቱን ገልጿል።
አለም አቀፍ የክርስቲያን ኢትዮጵያውያን እህቶች ህብረትም ንጹሃንን የገደሉ ለፍርድ እንዲቀርቡ ሲል ባወጣው መግለጫ ጠይቋል።
በብጹዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሪዎስ የሚመራው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ በኢትዮጵያ ሲካሄድ የቆየውን በተለይም በወልዲያና በቆቦ አሁንም የቀጠለውን ግድያ በማውገዝ ባለ 6 ነጥብ መግለጫ አውጥቷል።
በመላ ኢትዮጵያ ለተገደሉትም በየአብያተክርስቲያናቱ ጸሎተ ፍትሃት እንዲደረግ ወስኗል።
ለሟች ቤተሰቦችም መጽናናትን በመመኘት ለተፈናቃይ ኢትዮጵያውያንም ድጋፍ እንዲደረግ ጥሪ አቅርቧል።
የመከላከያ ሰራዊት አባላትም በወገኖቻቸሁ ላይ ከመተኮስ ታቀቡ፣በወንጀል ከመጠየቅም ራሳችሁን አድኑ ሲል ቅዱስ ሲኖዶሱ በመግለጫው ጠይቋል።
የፖለቲካ ሃይሎችም ተባብረው ህዝባቸውን እንዲታደጉም አሳስቧል።
የኢትዮጵያም ሕዝብ በእምነትም ሆነ በብሄር ሳይለያይ በአንድነት እንዲቆምም ጥሪ አቅርቧል።
የኢትዮጵያ ሙስሊሞች ንቅናቄ ሕብረት በበኩሉ በወልዲያና በቆቦ የተፈጸመውን ግድያ አውግዟል።
“በሰላማዊ መንገድ በአላቸውን በሚያከብሩት የኦርቶዶክስ የወልዲያ ወገኖቻችን ላይ የተፈጸመውን አሰቃቂ ግድያ በጽኑ እናወግዛለን”ሲልም ገልጿል።
ከዚህ ቀደም በሙስሊም ኢትዮጵያውያን ላይ በኮፈሌ በአሳሳ፣በአንዋር መስጊድና በገርባ የተፈጸመውን ግድያም አስታውሷል።
ስልጣን ላይ ያለው መንግስት በሁሉም ኢትዮጵያውያን ላይ የተነሳ ጨካኝና ገዳይ ስርአት ነው ሲል ገልጿል።
አለም አቀፍ የክርስቲያን እህቶች ህብረት ባወጣው መግለጫ በሀገር ውስጥም ሆነ በውጭ ያሉ ወንጌላውያን ይህንን ግድያ እንዲያወግዙ ጥሪ አቅርቧል።
በግፍ ለተጨፈጨፉት ወገኖቻችንም ሀዘናችንን እንገልጻለን ብሏል።
ይህን ግድያ የሚፈጽሙና የሚያስፈጽሙ ከድርጊታቸው እንዲታቀቡ፣በጭፍጨፋው ተጠያቂ የሆኑም ለፍርድ ይቅረቡ ሲል ጥሪ አቅርቧል።
መግለጫው ሲያጠቃልልም በተለይም የወንጌላውያን አማኞች ቤተክርስቲያን ዝምታን መምረጣቸው ተገቢ ነው ብለን ስለማናምን በኢትዮጵያ ውስጥ ሆነ በውጭ ያሉት አብያተ ክርስቲያናት ይህንን አሳዛኝ ድርጊት እንዲኮንኑት እንጠይቃለን በማለት ጥሪውን አስተላልፏል።