ነብይ ነኝ ባዩ ናይጄሪያዊ በቁጥጥር ስር ዋለ

(ኢሳት ዲሲ–ጥር 17/2010)

ነብይ ነኝ ባዩ ናይጄሪያዊ አደንዛዥ እጽ ሲያዘዋውር በቁጥጥር ስር መዋሉን የዛምቢያ ፖሊስ ገለጸ።

የ42 አመቱ ናይጄሪያዊ አይዛክ ጁልየስ አማታ በዛምቢያ ርዕሰ መዲና ሉሳካ በቁጥጥር ስር የዋለው ዛሬ መሆኑ ታውቋል።

26 ኪሎ ግራም አደንዛዥ እጽ እንደተገኘበትም ቢቢሲ በዘገባው አስፍሯል።

ሉሳካ ኬኔት ካውንዳ አውሮፕላን ማረፊያ ሲደርስ በቁጥጥር ስር የዋለው አይዛክ ኦማታ ወደ እስር ቤት መወሰዱም ታውቋል።

በእጽ አዘዋዋሪነትም እንደሚከሰስ ይፋ ሆኗል።

የዛምቢያን ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ አስቀድሞ በመተንበይ ኤድጋር ሉንጎ ፕሬዝዳንት ይሆናሉ በማለቱ በአንዳንድ ዛምቢያውያን ዘንድ ይታመን እንደነበርም አንዳንድ ዘገባዎች አመልክተዋል።