(ኢሳት ዲሲ–ጥር 17/2010)
ከከፍተኛ የትምህርት ተቋማትና ዩኒቨርስቲዎች በተለያዩ ምክንያቶች ጊዜያዊ የትምህርት ማቋረጥ(ዊዝድሮዋል) የጠየቁ ተማሪዎች የመልሶ ቅበላ እንደማይፈቀድላቸው የመንግስት ቃል አቀባይ ገለጹ።
ቃል አቀባዩ ዊዝድሮዋል መሙላት ቴክኒካል ጉዳይ ነው ሲሉም ተደምጠዋል።
የመንግስት ቃል አቀባዩ ዶክተር ነገሬ ሌንጮ በጽሕፈት ቤታቸው ለመንግስት፣ለፓርቲና ለግል መገናኛ ብዙሃን በሰጡት መግለጫ ላይ የዩኒቨርስቲ ተማሪዎች የጊዜያዊ ትምህርት ማቋረጥ(ዊዝድሮዋል) መሙላት አይችሉም ሲሉ ተደምጠዋል።
ቃል አቀባዩ በ2010 ጊዜያዊ ማቋረጥን መሙላት የማይችሉት በዩኒቨርስቲዎች የታየው የጸጥታ ስጋት በቁጥጥር ስር በመዋሉ ነው ሲሉ ምክንያቱን አስቀምጠዋል።
የጸጥታ ችግሩን የፈጠሩት ተማሪዎች በቁጥጥር ስር ውለዋል፣ወደፊትም የቀሩትን በቁጥጥር ስር ለማዋል መንግስት እየሰራ እንደሆነ ገልጸዋል።
ዊዝድሮዋል መሙላት ቴክኒካል ጉዳይ ነው ያሉት ዶክተር ነገሬ ሌንጮ መንግስት ዩኒቨርስቲዎችን እያስፋፋ ያለው የሀገር ተረካቢ የሆኑ ዜጎችን ለማፍራት እንጂ ወደ ቤተሰብ ተመልሰው ሽክም እንዲሆኑ አይደለም በማለት ተናግረዋል።
ኢሳት በዚህ የመንግስት ውሳኔ ላይ አስተያየት እንዲሰጡ የጠየቃቸው የዩኒቨርስቲ መምህራን ይህ የመንግስት ውሳኔ የዩኒቨርስቲዎችን ፖሊሲ የሚቃረን ከመሆኑም በላይ የተማሪዎችን መብት የሚጥስ እንደሆነ ገልጸዋል።
የተማሪዎች መብትና ግዴታ በሰፈረባቸው የዩኒቨስቲዎች ፖሊሲ ውስጥ ተማሪዎች በተለያየ ምክንያት በጊዜያዊነት ትምህርታቸውን ዊዝድሮዋል በመሙላት ሊያቋርጡ እንደሚችሉ መስፈሩን መምህራኑ ይናገራሉ።
በአሁኑ ሰአት በመላው ኢትዮጵያ እየታየ ያለው ስጋት በዩኒቨርስቲዎች ጎላ ብሎ ስለሚታይ በርካታ ተማሪዎች ተረጋግተው እንዳይማሩ የስነ ልቦና ጫና እንደሚያሳድር የማይደበቅ እውነታ ነው።
ይህ እየታወቀ ዊዝድሮዋል አንፈቅድም ማለት ግን ጭንቀት የወለደው የፖለቲካ ውሳኔ እንደሆነ ምሁራኑ አክለው ገልጸዋል።