(ኢሳት ዲሲ–ጥር 17/2010)
በሰሜን ወሎ ቆቦ ትላንት የተጀመረው ህዝባዊ አመጽ ዛሬ ተባብሶ መቀጠሉ ታወቀ።
የአጋዚ ሰራዊት በወሰደው ርምጃ 9 ሰዎች መገደላቸውን የኢሳት ምንጮች ገልጸዋል።
አንድ የአጋዚ ወታደርም መገደሉ ታውቋል።
ህዝቡ ራሱን ለመከላከል ከዘመተበት የህወሃት ጦር ጋር መጋጠሙ ይነገራል።
ከህወሃትና ብአዴን ጋር ግንኙነት ያላቸው ግለሰቦች ንብረቶች ላይ ርምጃ እየተወሰደ ነው።
የመንግስት መስሪያ ቤቶች፣ ፍርድ ቤት፣ 4 ቀበሌዎች መቃጠላቸውን በቪዲዮ ተደግፎ ለኢሳት ከደረሰው መረጃ ለማወቅ ተችሏል።
በቆቦና ዙሪያዋ የህዝብ አመጽ ተጠናክሮ በቀጠለበት በዛሬው ዕለት የህወሃት አገዛዝ ተጨማሪ ሃይል እያሰማራ ነው። ህዝቡ መንገዶችን ዘግቷል።
የወልዲያው ጭፍጨፋ ቆቦን ሰላም ነስቷታል።
በ50ኪሎ ሜትር የምትርቀው ቆቦ ካለፈው ቅዳሜ ጀምሮም ሰላም የነሳት ጉዳይ የታመቀ የህዝብ ቁጣ ዳር ዳር እንዲልባት አደረገና ትላንት ፈነዳ።
በህወሃት አገዛዝ በግፍ የተገደሉ የወልዲያ ሰማዕታትን በማስታወስ የተጀመረው ህዝባዊ አመጽ ከስርዓቱ ጋር ግንኙነት ያላቸውን ግለሰቦች ንብረቶቻቸው ላይ ጥቃት በመሰንዘር ቀጠለ።
ከመንግስት መስሪያ ቤቶች የቆቦ ከተማ ማዘጋጃ ቤት፣ የገቢዎች መስሪያ ቤት፣ የከተማዋ ፍርድ ቤት፣እንዲሁም 4ቱ የቀበሌ ጽ/ቤቶች በከፊልና ሙሉ በሙሉ ተቃጠሉ።
ከህወሀትና ብአዴን ጋር ግንኙነት ያላቸው ግለሰቦች ንብረቶች ላይም ርምጃ ተወስዷል።
ሶስት ተሽከርካሪዎች በከተማዋ የተለያዩ ቦታዎች ሲቃጠሉ ከቆቦ መውጪያ ላይ አራት የዳሽን ቢራ ከባድ ተሽከርካሪዎች ርምጃ ተወስዶባቸው ወድመዋል።
ለኢሳት በደረሰው የቪዲዮ ምስል ላይ እንደተረጋገጠው ከፍተኛ ቁጥር ያለው የአጋዚ ሰራዊት በቆቦ ከተማ ተሰማርቷል።
ከትላንት ጀምሮ ከትግራይ የገቡ የአጋዚ ሰራዊት አባላት በቆቦ ነዋሪ ላይ መጠነ ሰፊ ጥቃት የከፈቱ ሲሆን ህዝቡም ራሱን ለመከላከል የአጸፋ ርምጃ በመውሰድ ላይ ነው።
በእስከአሁኑ ሂደትም 9 የቆቦ ነዋሪዎች በአጋዚ ጦር ሲገደሉ ህዝቡ በአጸፋው አንድ ወታደር መግደሉን የደረሰን መረጃ አመልክቷል።
ወደ ቆቦ የሚወስዱ መንገዶች በየቦታው በድንጋይና በግዙፍ እንጨቶች በመዘጋታቸው በተሽከርካሪ መድረስ ያልቻለው የመከላከያ ሰራዊቱ በሄሊኮፕተር ከሰማይ በመውረድ የአጋዚን ሰራዊት መቀላቀሉም ታውቋል።
የሄሊኮፕተሩ እንቅስቃሴ በነዋሪው ላይ የስነልቦና ሽብር ለመፍጠር የታሰበ እንደሆነ ይነገራል።
ከዚሁ ጋር ተያይዞ የተፈጠረው ሌላው ክስተት ደግሞ ቆቦ በደረሰው የመከላከያ ሰራዊት መካካል የእርስ በእርስ ግጭት መፈጠሩ ነው።
መከላከያ ሰራዊቱ በትግራይና በሌሎች አባላት መካከል ኖክ በተባለው አካባቢ የተኩስ ልውውጥ መደረጉን የኢሳት ምንጮች ከስፍራው አረጋግጠዋል።
የአማራና የኦሮሞ ተወላጅ የሆኑ የመከላከያ ሰራዊት አባላት በህዝቡ ላይ አንተኩስም ማለታቸው ደግሞ ለእርስ በእርሱ ግጭቱ ምክንያት ተደርጎ ተጠቅሷል።
በዚህም በርካታ ወታደሮች ተጎድተው በሄሊኮፕተር ከአካባቢው መወሰዳቸው ታውቋል። የሞቱ ወታደሮች እንዳሉ ቢታወቅም ቁጥራቸው ለጊዜው አልተገለጸም።
የሰራዊቱ የእርስ በርስ ግጭት መፍትሄም ሲያጣ ሕወሃት ህዝቡ ላይ እንዲወሰድ የታቀደውን ርምጃ በብቸኝነት የተሳተፈው የአጋዚ ጦር መሆኑ ታውቋል።
በሌላ በኩል ቁጥራቸው ከ100 በላይ የሚሆኑ የአላማጣ ወጣቶች የዶክተር ደብረጺዮን ገብረሚኤልን ፎቶግራፍ እያቃጠሉ ለቆቦ ነዋሪዎች ድጋፋቸውን ለመስጠት ወደ ቆቦ ማምራታቸው ታውቋል።
በጎብዬ፣ ሮቢትና በሌሎች በቆቦ ዙሪያ ያሉ መንደሮች ከፍተኛ ውጥረት እንዳለ ይነገራል።
ወደ ቆቦ የሚወስዱ መንገዶች ተዘግተዋል። ትምህርት ቤቶችና ንግድ ቤቶችም እንደተዘጉ ናቸው።
አሁንም አልፎ አልፎ የተኩስ ድምጽ እንደሚሰማ ለማወቅ ተችሏል።