(ኢሳት ዲሲ–ጥር 17/2010)
የሕዝባዊ ወያኔ ሃርነት ትግራይ/ሕወሃት/ንብረት የሆነው ሰላም ባስ በወልዲያ በተቀሰቀሰው ሕዝባዊ ቁጣ የቀየረውን የጎዞ መስመር በአፋር ክልል በገጠመው የጸጥታ ችግር እንደገና ለሁለተኛ ጊዜ ለመቀየር መገደዱን አስታወቀ።
በዚህም በመቶዎች የሚቆጠሩ ተጨማሪ ኪሎ ሜትሮችን መጓዝ ግዴታ ስለሆነበት የታሪፍ ማስተካከያ ማድረጉን ይፋ አድርጓል።
የሕዝባዊ ወያኔ ሃርነት ትግራይ /ሕወሃት/ንብረት የሆነው ሰላም ባስ ጥር 15/2010 “ለተከበራችሁ ደንበኞቻችን” በሚል ያወጣው ማስታወቂያ ከአዲስ አበባ መቀሌና ከአዲስ አበባ ሽሬ የሚደረገው ጉዞ በጸጥታ ምክንያት የስምሪት መስመሩ ተቀይሯል ሲል ይገልጻል።
የስምሪት መስመሩ ለውጥ አውቶቡሶቹን ተጨማሪ 217 ኪሎ ሜትር እንዲጓዙ ስለሚያደርጋቸውና በአጠቃላይ 1ሺ ኪሎ ሜትር በመሆኑ የታሪፍ ማስተካከያ ለማድረግ መገደዱንም ባወጣው ማስታወቂያ ላይ አመልክቷል።
በዚህም መሰረት ከአዲስ አበባ መቀሌ 485 ብር የነበረው ታሪፍ 620 ብር ሲገባ ከአዲስ አበባ ሽሬ ደግሞ 805 ብር እንደሆነና ይህም ከነገ አርብ ጀምሮ ተግባራዊ እንደሚሆን አስታውቋል።
የሕወሃት ንብረት የሆነው ሰለም ባስ በወልዲያ በተቀሰቀሰ ሕዝባዊ ቁጣ ሳቢያ ጉዞውን በአፋር ክልል በጭፍራ በኩል ለቀናት ማካሄዱ ተመልክቷል።
ሆኖም ከዚያም በኩል የጸጥታ ችግር በማጋጠሙ ጉዞውን በአፋር ክልል ዋና ከተማ ሰመራ በኩል እንዲሆን ማደረጉንም ለደንበኞቹ ከበተነው ማስታወቂያ ላይ መመልከት ተችሏል።
ሕዝባዊ ወያኔ ሃርነት ትግራይ/ሕወሃት/ ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ያለመያዣ በተበደረውና በኋላም ባስቀረው 2 ቢሊየን ብር ከተቋቋሙ የፓርቲው ኩባንያዎች አንዱ መሆኑ ይታወቃል።
ይህ አውቶቡስ በኢትዮጵያ የተለያዩ አካባቢዎች በሚያደርገው ጉዞ ለጥቃት ሲጋለጥ መቆየቱም ይታወሳል።
በቅርቡም በቁልቢ ገብርኤል ክብረ በዓል ላይ የሚታደሙ ምዕመናንን ይዞ ሲጓዝ ስርዓቱን የሚቃወሙ ወጣቶች ምዕመናኑን እንዲወርዱ ካደረጉ በኋላ አውቶቡስን መሰባበራቸውን መዘገባችን ይታወሳል።