(ኢሳት ዲሲ–ጥር 15/2010)
የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ አመራር ቦርድ የሕወሃቱን እጩ ፕሮፌሰር ጣሰው ወልደሃና ካህሳይን ጨምሮ 3 እጩዎችን ለትምህርት ሚኒስቴር አስተላለፈ።
ለአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ፕሬዝዳንትነት በኦሕዴድ ከታጩት ፕሮፌሰር በቀለ ጉተማ ጀቤሳ በተጨማሪ ዶክተር ጄይሉ ኡመር ሁሴንም በእጩዎች ውስጥ ተካተዋል።
ለዩኒቨርስቲው ፕሬዝዳንትነት ሕወሃትና ኦህዴድ መፋጠጣቸውን የኢሳት ምንጮች ገልጸዋል።
የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ፕሬዝዳንትን ለመምረጥ ብቃትን መሰረት ባደረገ መልኩ ውድድር እየተካሄደ መሆኑ ሲገለጽ ቆይቷል።
ይህም ሆኖ ግን ሕወሃት የራሱን እጩ ለማስመረጥ ፕሮፌሰር ጣሰው ወልደሃና ካህሳይን አሸናፊ ለማድረግ ጣልቃ እየገባ መሆኑን የኢሳት ምንጮች አረጋግጠው ነበር።
እንዳሉትም አልቀረ ፕሮፌሰር ጣሰው በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ቦርድ ከተመረጡ ሶስት ተመራጭ እጩዎች አንዱ ሆነዋል።
በኦሕዴድ በኩል ከፍልስፍና ዲፓርትመንት ፕሮፌሰር በቀለ ጉተማ የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ፕሬዝዳንት እንዲሆኑ ግፊት ሲደረግ ነበር።
እሳቸውም ከ3ቱ እጩዎች መካከል አንዱ መሆናቸው ታውቋል።
በ3ኛ ደረጃ ተመርጠው ለትምህርት ሚኒስቴር ከተላኩት እጩዎች ሌላኛው ደግሞ ዶክተር ጄይሉ ኡመር ናቸው።
22 እጩዎች ለውድድር ከቀረቡ በኋላ ዘጠኙ ለ2ኛ ዙር አልፈው አሁን ደግሞ 3ቱ በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ቦርድ ተመርጠው ለትምህርት ሚኒስቴር ተልኳል።
ትምህርት ሚኒስቴር በበኩሉ ከ3ቱ እጩዎች አንዱን በመምረጥ ፕሬዝዳንት አድርጎ ይሾማል።
በሕወሃት በኩል የቀረቡት በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የኢኮኖሚክስ ዲፓርትመንት ሃላፊ የነበሩት ፕሮፌሰር ጣሰው ወልደሃና ካህሳይ ፕሬዝዳንት ይሆናሉ ተብሎ እየተጠበቀ ነው።
በሌላ አንጻር በኦህዴድ በኩል ተመራጭ የተደረጉት ፕሮፌሰር በቀለ ጉተማ ደግሞ ሌላው ተፎካካሪ ናቸው ተብሏል።
እናም ምርጫውና ፉክክሩ በሕወሃትና በኦሕዴድ መካከል ሆኗል ነው የተባለው።
ለአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ፕሬዝዳንትነት እየተወዳደሩ ከነበሩት መካከል የጠቅላይ ሚኒስትር ሃይለማርያም ደሳለኝ ወንድም ፕሮፌሰር ፍቅሬ ደሳለኝ ተመራጭ ሳይሆኑ መቅረታቸውን ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።