(ኢሳት ዲሲ–ጥር 15/2010)
የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ባለስልጣን የሚባለውንና ለመገናኛ ብዙሃን ፈቃድ የሚሰጠውን ተቋም ሙሉ በሙሉ የሚመሩት የሕዝባዊ ወያኔ ሀርነት ትግራይ አባላት መሆናቸው ተጋለጠ።
የሕወሃትን ቀውስ ተከትሎ እየተበተነ ያለው መረጃ በኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን የሚሰሩ እንዲሁም በግል መገናኛ ብዙሃን የሚሳተፉ የሕወሃት አባላት ዝርዝርም ይፋ ሆኗል።
በኢትዮጵያ በግል እንዲሁም በማህበረሰብ ለሚሰሩ ሬዲዮና ቴሌቪዥን እንዲሁም የሕትመት ሚዲያዎች ፈቃድ የሚሰጠው የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ባለስልጣን የተባለውን ተቋም የሚመሩት አቶ ዘርአይ አስገዶምን ጨምሮ ከፍተኛ ሃላፊዎቹ የሕወሃት አባላት መሆናቸው ተመልክቷል።
በሰነዱ ላይ እንደተዘረዘረው ከዋና ዳይሬክተሩ አቶ ዘርአይ አስገዶም በተጨማሪ ምክትል ዳይሬክተሩ አቶ ልኡል ገብሩ ገብረእግዚአብሔር እንዲሁም ገብረጊዮርጊስ አብርሃ ካህሳይ በዳይሬክተርነት ተቋሙን በበላይነት ሲመሩ ገነት ገብረ አየል፣ጌታቸው ግርማይ የማነ፣ብርሸዋ ስዩም ታፈረና ሃፍቶም ግብረስላሴ ገብረጊዮርጊስ በከፍተኛ ባለሙያነት በዚሁ ተቋም ውስጥ የሚያገለግሉ የህወሃት አባላት መሆናቸው ተጋልጧል።
በእነዚህ የህወሃት አባላት የሚመራው የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ባለስልጣን ከወራት በፊት የህወሃት ንብረት ለሆኑት ሬዲዮ ፋናና ዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል የቴሌቪዥን ጣቢያ ፈቃድ መስጠቱ ይታወሳል።
ከብሮድካስት ባለስልጣን ሃላፊዎች በተጨማሪ በመንግስታዊ ተቋማት እንዲሁም በግል መገናኛ ብዙሃን የሚሳተፉ የሕወሃት አባላት ስም ዝርዝርም በዚህ ባለ 6 ገጽ መረጃ ላይ ይፋ ሆነዋል።
በዚህ መረጃ መሰረትም በኢትዮጵያ ሬዲዮና ቴሌቪዥን ከሚሰሩ ጋዜጠኞች 67ቱ የሕወሃት አባላት ሲሆኑ በስምና በእድሜ እንዲሁም አባል የሆኑበት አመት በዝርዝር ተያይዞ ቀርቧል።
በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ውስጥ ደግሞ ዳይሬክተሩን አቶ ነጋሲ አምባዬን ጨምሮ 8 ያህል ጋዜጠኞችና ሃላፊዎች የህወሃት አባልነትን ቅጽ የሞሉና በአባልነት የታቀፉ መሆናቸው ይፋ ሆኗል።
በግል ሚዲያ ከሚንቀሳቀሱትና በማህበራዊ መድረክ በሕወሃት ደጋፊነት ከሚንቀሳቀሱት ውስጥ የሆርን አፌርስ ድረገጽና የአውራምባ ድረገጽ አዘጋጆች አቶ ዳንኤል ብርሃነንና አቶ ዳዊት ከበደን ጨምሮ የሌሎችም የሕወሃት አባላት ዝርዝር በዚሁ ሰነድ ተመልክቷል።
ይሔ ዝርዝር በፌደራል መንግስት ተቋማትና በአዲስ አበባ የተወሰኑትን የሚመለከት እንደሆነም ማወቅ ተችሏል።
በአማራ ክልል እንዲሁም በደቡብ ክልልና በሌሎች መገናኛ ብዙሃን ውስጥ የሚሰሩት የህወሃት አባላት ዝርዝር ግን በዚሁ ባለ 6 ገጽ ሰነድ ውስጥ አልተካተተም።
በተመሳሳይ በትግራይ ክልል ቴሌቪዥንም ሆነ በሌሎች የትግራይ ክልል መገናኛ ብዙሃን ውስጥ የሚሰሩትንም ዝርዝር አልጨመረም።