(ኢሳት ዲሲ–ጥር 14/2010)
የመላው አማራ ሕዝብ ድርጅት /መኢሕድ/ አለም አቀፍ ድጋፍ ሰጪና የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረስ አለም አቀፍ የድጋፍ ትብብር በጋራ ለመስራት የሚያስችላቸውን ስምምነት ተፈራረሙ።
የሁለቱ ድጋፍ ሰጭ የስራ አመራር አባላት በቨርጂኒያ ሒልተን ሆቴል ባደረጉት የስምምነት ስነ ስርአት ላይ እንደተገለጸው ፓርቲዎቹ የሕወሃትን ስርአት ለመለወጥ በጋራ ለመስራት ይተባበራሉ።
በዚሁም የዲፕሎማሲ ጥረቶችን በጋራ ለማከናወን በአገዛዙ ላይ የሚካሄዱ ተቃውሞዎችን በትብብር ማካሄድና ጥቃት በአንደኛው ማህበረሰብ ላይ ሲፈጸምም በሕብረት ለማውገዝ ተስማምተዋል።
ስምምነቱ ያስተባበሩት ለረጅም አመታት የሕወሃትን አገዛዝ በመቃወም የሚታወቁት ዴቪድ ስታይንማን ጠላትን ለማስወገድ መተባበር ያስፈልጋል ብለዋል።
ለድህነትና ለጭቆና ምክንያት የሚሆነው መከፋፈል ሲኖር ብቻ በመሆኑ የሁለቱ ድርጅቶች መተባበር ከፍተኛ ለውጥ እንደሚያመጣ ዴቪድ ስታይንማን ገልጸዋል።
በሁለቱ ድርጅቶች የትብብር ድጋፍ ሰጭ ስራ አስፈጻሚ አባላት መካከል የተደረገውን ስምምነት አቶ ኔጌሶ ኦዳ የኦፌኮ አለም አቀፍ ድጋፍ ሰጭ አስተባባሪና በመኢህድ በኩል ደግሞ የድርጅቱ አለም አቀፍ የድጋፍ ኮሚቴ ሊቀመንበር አቶ መንግስቱ አስፋው ናቸው።