አቶ ስዬ አብርሃ ሀገር ቤት ገቡ

(ኢሳት ዲሲ–ጥር 14/2010)

በሕዝባዊ ወያኔ ሃርነት ትግራይ ውስጥ የተፈጠረው ቀውስ መፍትሄ ባላገኘበት በአሁኑ ወቅት አቶ ስዬ አብርሃ ሀገር ቤት መግባታቸው ታወቀ።

በአቶ ስብሃት ነጋ የሚደገፈው የዶክተር ደብረጺዮን ቡድን በአቶ አባይ ወልዱ ቡድን ላይ የጀመረውን ጥቃት በመቀጠልም ወይዘሮ አዜብ መስፍንን ከኤፈርት ሃላፊነት ማንሳቱንም የሕወሃት ደጋፊ የመረጃ ማዕከላት ዘግበዋል።

ከአንጋፋዎቹ የሕወሃት ታጋዮች አንዱ የነበሩትና የሕወሃት ጦር አዛዥ በኋላም የመከላከያ ሚኒስትር ሆነው ያገለገሉት አቶ ስዬ አብርሃ ከሁለት ሳምንት በፊት ኢትዮጵያ መግባታቸውን የኢሳት ምንጮች አረጋግጠዋል።

አቶ ስዬ አብርሃ ወደ ኢትዮጵያ የገቡት በወንድማቸው ስም የተሰራውን ትምህርት ቤት ለመመረቅ እንደሆነ ተገልጿል።

ነገር ግን አቶ ስዬ አብርሃ ከሕወሃት አንጋፋ መሪዎች ጋር መገናኘታቸው ተሰምቷል።

አቶ ስዬ አብርሃ በደርግ መንግስት በቀይ ሽብር በተገደለው ወንድማቸው ገብረስላሴ አብርሃ ስም የተሰራውን ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ለመመረቅ ወደ ትግራይ ክልል መሄዳቸውን ቢገልጹም ከነጄኔራል ጻድቃን ገብረተንሳይ እንዲሁም ከጄኔራል አበበ ተክለሃይማኖትና ከሌሎች የሕወሃት ሰዎች ጋር መገናኘታቸውም ታውቋል።

የሕወሃት ታጋይ የነበሩት ሌተናል ጄኔራል ጻድቃን ገብረተንሳይና ሜጀር ጄኔራል አበበ ተክለሃይማኖት ከአቶ ስብሃት ነጋ ጋር በቅርበት በመስራት ላይ እንደሆኑ ምንጮቹ ይገልጻሉ።

እንደ ምንጮቹ ከሆነ አቶ ስዬ አብርሃ ከአቶ ስብሃት ነጋና ከሌሎችም የህወሃት መሪዎች ጋር ሳይመክሩ አልቀረም።

አቶ ስዬ አብርሃ በወንድማቸው በገብረስላሴ አብርሃ ስም የተሰየመውን የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ሲያስመርቁ ሁለቱ የሕወሃት ጄኔራሎች መገኘታቸውም ታውቋል።

የሕዝባዊ ወያኔ ሃርነት ትግራይ/ሕወሃት/ አመራር ለሁለት ሲሰነጠቅ አቶ ስዬ አብርሃ በሙስና ተወንጅለው ከወንድምና እህቶቻቸው ጋር ወደ ወህኒ መጋዛቸው ይታወሳል።

ከ5 አመታት እስራት በኋላ ሲለቀቁ ከዶክተር ነጋሶ ጊዳዳ ጋር በመሆን አንድነት ፓርቲን ተቀላቅለው በአመራር አባልነት ሲሳተፉ ቆይተዋል።

ለትምህርት በሚል ወደ አሜሪካ እንደወጡ የፖለቲካ ተሳትፏቸው እየቀነሰ የመጣውና ከነ ቤተሰባቸው መኖሪያቸውን በአሜሪካ ዴንቨር ከተማ ያደረጉት ስዬ አብርሃ ከ6 አመታት ወዲህ ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ ኢትዮጵያ መሄዳቸውንም መረዳት ተችሏል።

ሕዝባዊ ወያኔ ሃርነት ትግራይ/ሕወሃት/ ውስጣዊውን ቀውስ እንዲሁም ውጫዊውን ግፊት ለመቋቋም ቀደም ሲል በተለያየ መንገድ የለቀቁ አመራሮቹን ለማሰባሰብ ጥረት እያደረገ ይገኛል።

የሕወሃት ሰራዊት አዛዥ በኋላም በሽግግሩ መንግስት የመከላከያ ሚኒስትር የነበሩት አቶ ስዬ አብርሃ የዚህ ሂደት አካል ይሁኑ አይሁኑ ለጊዜው ማረጋገጥ አልተቻለም።

ሕዝባዊ ወያኔ ሃርነት ትግራይ ሕወሃት ለሁለት ሲሰነጠቅ የኤፈርት ስራ አስኪያጅ የነበሩት አቶ ስዬ አብርሃ ከቀረቡባቸው ክሶች አንዱ መንግስት ለኤፈርት ያደረገውን ቅናሽ በመጠቀም ወንድማቸውን የከባድ መኪና ባለንብረት አድርገዋል የሚል እንደነበርም ማስታወስ ተችሏል።

ይህ በእንዲህ እንዳለም አሁን ላይ ኤፈርትን በሃላፊነት ሲመሩ የነበሩት ወይዘሮ አዜብ መስፍን ከኤፈርት ሃላፊነት ቦታቸው መነሳታቸውን የሕወሃት ደጋፊ የመረጃ ምንጮች አስታውቀዋል።

በወይዘሮ አዜብ መስፍን ላይ የተወሰደው ርምጃ በአቶ ስብሃት ነጋ የሚደገፈው የዶክተር ደብረጺዮን ቡድን በአቶ አባይ ወልዱ ቡድን ላይ የጀመረውን ጥቃት መቀጠሉን ያረጋገጠ ነው ተብሎለታል።