(ኢሳት ዲሲ–ጥር 11/2010)
በየዓመቱ ጥር 11 የሚከበርው የጥምቀት በዓል በመላው ዓለም በሚገኙ የክርስትና እምነት ተከታዮች ዘንድ በድምቀት ተከበረ።
በኢትዮጵያ በበዓሉ አከባበር ላይ ስርዓቱን የሚቃወሙ ድምጾች በብዛት መሰማታቸው ታውቋል።
በኦርቶዶክስ እምነት ተከታዮች ዘንድ በድምቀት ከሚከበሩ በዓላት መካከል አንደኛው የጥምቀት በዓል ነው። በዘንድሮው የጥምቀት በአልም በርካታ የእምነቱ ተከታዮች በዓሉ በሚከበርባቸው ቦታዎች በመገኘት ሃይማኖታዊ ስነስርዓቱን ተካፍለዋል።
በበዓሉ ዋዜማ በሚከበረው የከተራ በዓልም ታቦታቱ ከየደብራቸው በመውጣት ወደ ጊዜያዊ ማረፊያቸው ያጓዛሉ።
አዳራቸውም ከዛው ይሆናል። በስፍራውም ላይ ሀይማኖታዊ ስነስርዓቶች ሲከናወኑ ያድራሉ ።
በነጋታው ጥር 11 የሚውለውን የጥምቀት በዓል ተከትሎም የጸበል መርጨት ስነስርአት ከተከናወነ በኋላ ታቦታቱ ወደየስፍራቸው በምእመናን ታጅበው ይመለሳሉ።
ዛሬም በመላው ዓለም የሚገኙ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ እምነት ተከታዮች በዓሉን በድምቀት አክብረውት ውለዋል።
በኢትዮጵያ የበአሉ አከባበር ከሌላው ግዜ በተለየ መልኩ በፖሊስ፣በመከላከያና በደህንነት ሀይሎች ልዩ ጥበቃ ሲደረግለት እንደነበርም ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።
ኢሳት ያነጋገራቸው የበዓሉ ታዳሚዎች በተለይ በአዲስ አበባ ገዢው ስርዓት ተቃውሞ ይነሳብኛል በሚል ጥበቃው በአልሞ ተኳሾች ጭምር የታጀበ ነበር በማለት ድባቡ አስፈሪ ነበር ሲሉ ገልጸውታል።
በሌሎች የሀገሪቱ ከተሞች በዓሉ በድምቀት ሲከበርም ጎን ለጎን ከፍተኛ የተቃውሞ ድምጾች መሰማታቸውን ከደረሰን መረጃ መረዳት ችለናል።
በአምቦ፣ነቀምት፣ጎንደርና ወልዲያ በነበረው ክብረ በዓል ወያኔ ቻው ቻው የሚል የተቃወሞ መፈክር ጎልቶ ተሰምቷል።
በጎንደር ከተሰማው የህዝባዊ ተቃውሞ ድምጽ ውስጥ ኢትዮጵያ ለዘላለም በክብር ትኑር የሚለው መፈክር ለበዓሉ ልዩ ድምቀት ሰጥቶት እንደነበርም በምስል ተደግፎ ለኢሳት የደረሰው መረጃ ያመለክታል።
በዘንድሮው የጥምቀት በዓል ከሰሜን ደቡብ፣ ከምስራቅ ምዕራብ ምእመናኑ የኢትዮጵያን ሰነደቅ ዓላማ በብዛት በማውለብለብ ታቦታቱን ሲያጅቡ የያዙት ሰንደቅ ዓላማ ምንም ዓይነት ምልክት የሌለበትን አረንጓዴ ቢጫና ቀይ ቀለምን የተቀዳጀውን ባንዲራ እንደነበር ከወጡት ምስሎች መመልከት ተችሏል።
በተመሳሳይ በሌሎች ዓለማት የሚገኙ ኢትዮጵያውያን የእምነቱ ተከታዮችም በዓሉን በድምቀት አክብረዋል።
በአሜሪካ የተለያዩ ግዛቶች፣በአውሮፓ የተለያዩ ከተሞች፣ በደቡብ አፍሪካና በዱባይ በዓሉ በድምቀት ከተከበረባቸው መካከል የሚጠቀሱ ናቸው።
በሌላ በኩል የኦርቶዶክስ እምነት ተከታይ ሀገራትም በዓሉን በተመሳሳይ አክብረው ውለዋል።
ሩሲያ፣ግብጽ፣ግሪክና አርመን በዓሉ ከተከበርባቸው ሀገራት መካከል ናቸው።
በሩሲያ በነበረው ክብረ በዓል ላይም የሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን በባህረ ጥምቀቱ ታዳሚ ሆነው ታይተዋል።