የሕወሃትን አገዛዝ ለማዳከም የሚያስችሉ አቅጣጫዎችን የሚያሳይ ጥሪ ተላለፈ

(ኢሳት ዲሲ–ጥር 11/2010)

ኢትዮጵያውያን የውጭ ምንዛሪ ወደ ሀገር ውስጥ ባለመላክ የሕወሃትን አገዛዝ ለማዳከም የሚያስችሉ አቅጣጫዎችን የሚያሳይ ጥሪ ተላለፈ።

አለም አቀፍ የኢትዮጵያውያን የጋራ ግብረ ሃይል ለኢትዮጵያውያን ያስተላለፈው ጥሪ 3 መንገዶችን በመጠቀም የሕወሃትን አገዛዝ ማዳከም እንደሚቻል አመላክቷል።

አንደኛው ዌስተርን ዩኒየንና መኒግራምን ከመጠቀም ይልቅ ሌሎች አማራጮችን መጠቀም የሚል ነው።

በ2ኛ ደረጃ ደግሞ ሌሎች አማራጮች ካልተገኙና በባንክ በኩል መላክ የግድ ከሆነ የሚላከውን ገንዘብ መጠን መቀነስ እንደ አቅጣጫ ተቀምጧል።

በ3ኛ ደረጃ የተቀመጠው አቅጣጫ እንደሚያመላክተውም ለንግድ፣ ለግንባታና ገንዘብ ለማስቀመጥ ሲባል የሚላከው የውጭ ምንዛሪ ህወሃትን የሚያጠናክር በመሆኑ ለጊዜው ማቆም ይገባል።

በአለም አቀፍ የገንዘብ ድርጅት የቦርድ ዳይሬክተሮች መግለጫ መሰረት በኢትዮጵያ ያለው የህወሃት አገዛዝ የውጭ ምንዛሪ ክምችቱ ለ2 ወራት እንኳ የማይበቃ ነው።

እናም የኢትዮጵያን ሕዝብ ትግል ለማገዝ የውጭ ምንዛሪ ወደ ኢትዮጵያ ባለመላክ በውጭ የሚኖሩ ዜጎች ሁሉ እንዲተባበሩ ግብረሃይሉ ጥሪውን አስተላልፏል።