(ኢሳት ዲሲ–ጥር 11/2010)
በአዲስ አበባ ሳሊተ ምህረት ቅድስት ማርያም ቤተክርስቲያን የተፈጠረው ውዝግብ እንደቀጠለ መሆኑ ተሰማ።
ትላንት በጥምቀት በዓል ዋዜማ በአካባቢው የተኩስ እሩምታ እንደነበረ የደረሰን መረጃ አመልክቷል።
የፌደራል ፖሊስ የቤተክርስቲያኒቱ አገልጋዮችን በጅምላ በማፈስ ካሰረ በኋላ በህዝብ ተቃውሞ መፈታታቸው ታውቋል።
የቤተክርስቲያኒቱን ሀብትና ንብረት ከዘረፋ ለመታደግ ህዝቡ የጀመረውን ትግል ለማስቆም በህወሃት አገዛዝና በፓትርያርኩ የሃይል ርምጃ መወሰዱ ውጥረቱን እንዳባባሰው የኢሳት ምንጮች ገልጸዋል።
የውዝግቡ መነሻ ገንዘብና ሀብት ነው።
የሳሊተ ምህረት ቅድስት ማርያም ቤተክርስቲያን በአዲስ አበባ ከሚገኙ አብያተክርስቲያናትና አድባራት አንጻር ከፍተኛ ገቢ የምታገኝ፣ ከህዝበ ክርስቲያኑ በተለያየ መልኩ በሚለገሰው ገንዘብና ሀብት የተሻለ አቅም ያላት ቤተክርስቲያን ናት።
ይህ መሆኑ የተለያዩ ወገኖችን ትኩረት እንድትወሰድ አድርጓታል።
የኢሳት የቤተክህነት ምንጮች እንደሚሉት በሳሊተ ምህረት ቤተክርስቲያን የፓትርያርኩና ከህወሀት አገዛዝ ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት ያላቸው ሰዎች የተሳሰሩበት የጥቅም ሰንሰለት የውዝግቡ መንስዔ ሆኖ የሚጠቀስ ነው።
ከሌላ ቤተክርስቲያን ሙስና የተባረሩ ሰዎች በሳሊተ ምህረት እንዲሰገሰጉ ተደርገው በተለያየ መልኩ ለቤተክርስቲያኗ የሚገባውን የገንዘብና የወርቅ ሀብት እየዘረፉ መሆናቸውን የሚገልጹት የኢሳት ምንጮች በትዕግስት ሲጠባበቅ የነበረው ህዝበ ክርስቲያን በመጨረሻም ርምጃ መውሰድ መጀመሩን ይገልጻሉ።
የቤተክርስቲያኗ አስተዳዳሪ ከፓትሪያርክ አቡነ ማቲያስ ጋር ያላቸው የጥቅም ወዳጅነት ጉዳዩን እንዳወሳሰበው ይነገራል።
ከ250ሺህ ብር በላይ ወጪ የተደረገለት ዘመናዊ ጃኩዚ የተገጠመለት ውድ የሆነ መኖሪያ ቤት በቤተክርስቲያኗ ቅጥር ግቢ በማስገንባት ለፓትርያርኩ ማረፊያ ያደረጉት አስተዳዳሪው የፓትርያርኩን ስልጣን መከታ በማድረግ በቤተክርስቲያኗ ላይ መጠነ ሰፊ ዝርፊያ ሲያከናውኑ መቆየታቸውን ምዕመናን በቁጭት የሚያነሱት ጉዳይ ነው።
ከአንድ ወር በፊት በሽጉጥ ጭምር የሚያስፈራሩትን አስተዳዳሪውን በመደብደብ ከግቢ ያስወጣው ምዕመናን በህወሃት አገዛዝና በፓትርያርኩ የሚሰነዘርባቸውን ጥቃትና ጫና በመቋቋም የቤተክርስቲያኒቱን ዘረፋ ለማስቆም በመታገል ላይ እንደሆኑም ለማወቅ ተችሏል።
አስተዳዳሪው ወደ ቤተክርስቲያኒቱ ቅጥር ግቢ እንዳይደርሱ ሲከላከል የቆየው ህዝበ ክርስቲያኑ ከህወሃት አገዛዝ ታጣቂዎች ጋር በፍጥጫ ነው የከረመው።
የአስተዳዳሪውን ቢሮ ጨምሮ ገንዘብና ንብረት ያለባቸው ክፍሎች መታሸጋቸውን ተከትሎ ትላንት ቆጠራ ለማድረግ በተጀመረው ጥረት ውዝግብ መፈጠሩን የደረሰን መረጃ አመልክቷል።
የከተራን በዓል ከቤተክርስቲያኒቱ ቅጥር ግቢ ውጪ ለማክበር ታቦት ይዞ መውጣቱ ለዘራፊዎች ምቹ አጋጣሚ ይፈጥራል በሚል እዚያው በግቢው ለማክበር በምዕመናኑ ቢጠየቅም ከፖሊስ ጋር በተደረገ ስምምነት ግን ታቦት ወደ ማደሪያ እንዲሄድ ተደርጓል።
ሆኖም በመንገድ ላይ ከፌደራል ፖሊስ ጋር ግጭት መፈጠሩን የገለጹት የኢሳት ምንጮች በርካታ የቤተክርስቲያኒቱ አገልጋዮችና ምዕመናን መታሰራቸው የህዝቡን ቁጣ እንዳባባሰው ጠቅሰዋል።
ተቃውሞው ሲበረታም ፖሊስ ያሰራቸውን ወዲያውኑ መፍታቱን ለማወቅ ተችሏል። በወቅቱም የተኩስ እሩምታ እንደነበረ ተገልጿል።
ፓትርያርክ አቡነ ማቲያስ በህዝበ ክርስቲያኑ ተቃውሞ የቀረበባቸውን የቤተክርስቲያኗን አስተዳዳሪ በመደገፍና በመከላከል ምዕመኑን መዝለፋቸው ቁጣ ማስከተሉን የደረሰን መረጃ አመልክቷል።
የፌደራል ፖሊስ በቤተክርስቲያኒቱ ዙሪያ የተለየ ጥበቃ እያደረገ ሲሆን ህዝቡም በእምነታችን ላይ የመጣውን እስከሞት ዋጋ ለመክፈል ተዘጋጅተናል በማለት በአቋሙ ጸንቶ እንደሚገኝ ለማወቅ ተችሏል።