ከጸረ ሽብር ሕጉ የሚሰረዝም ሆነ የሚሻሻል አንቀጽ የለም

(ኢሳት ዲሲ–ጥር 10/2010)

ሕወሃት ኢህአዴግ ከጸረ ሽብር ሕጉ የሚሰረዝም ሆነ የሚሻሻል አንቀጽ እንደሌለ አስታወቀ።

በአንድ አንቀጽ ላይ ብቻ ማብራሪያ የሚሰጥ ተጨማሪ ህግ ይወጣል ብሏል።

ከጸረ ሽብር ሕጉ የሚሰረዝም ሆነ የሚሻሻል አንቀጽ እንደሌለ የተገለጸው ሕወሃት ኢሕአዴግ በጀት ከሚመድብላቸውና ታማኙ ከሆኑ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር ባደረገው ውይይት ላይ ነው።

በዚህ ውይይት ገዢው ፓርቲ በስራ ላይ ያለው ጸረ ሽብር ህግ በምንም አይነት ከአለም አቀፍ ህጎች ጋር እንደማይጻረር፣ከሕገ መንግስቱ ጋር እንደሚጣጣም እንዲሁም ከወንጀለኛ ህጉ ጋር የማይቃረን በመሆኑ የትኛውም አንቀጾች እንደማይሰረዙ አስታውቋል።

የሽብር ተጠርጣሪዎችን ፖሊስ በሚይዝ ሰአት ተመጣጣኝ ሃይል መጠቀም አለበት የሚለው አንቀጽ ብቻ ማብራሪያ የሚሰጥ ተጨማሪ ህግ እንደሚወጣ አስታውቋል።

ይሄም በጸረ ሽብር ህጉ ላይ የሚደረግ ማሻሻያ ተደርጎ ሊወሰድ ይገባል ብሏል።

በጉዳዩ ላይ ለኢሳት አስተያየታቸውን የሰጡ የፖለቲካ ምሁራን እንደገለጹት ገዥው ፓርቲ ጸረ ሽብር ህጉን የመሳሰሉ ጨቋኝ ሕጎች እንዲሰረዙ ፍላጎት የሌለው የፖለቲካ ምህዳሩን ማስፋት ስለማይፈልግ ነው።

ይህ የዛሬ አቋሙ በተከታታይ ከሰጠው ድርጅታዊ መግለጫዎቹም ጋር እንደሚጣረስ ጨምረው ገልጸዋል።

የኢሕአዴግ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ በሰጠው ድርጅታዊ መግለጫ ዲሞክራሲውን ማስፋትና ማጠናከር ሲገባ በተለያዩ መንገዶች የማጥበብ አዝማሚያዎች መስተዋላቸውን፣የሲቪክ ማህበረሰብ ተሳትፎና ሁለገብ እንቅስቃሴ ገደብ ከጣሉበት ችግሮች በማላቀቅ ማጠናከር እንደሚገባ መተማመን ላይ መደረሱን ገልጾ ነበር።

መግለጫው አያይዞም በኢትዮጵያ የመድብለ ፓርቲ ዲሞክራሲያዊ ስርአት ችግር የገጠመው በሕወሃት/ኢሕአዴግ/ ዳተኝነት በመሆኑ ችግሩን በጊዜና በአግባቡ ተገንዝቦ ተገቢውን ህጋዊ ርምጃ እንደሚወስድ ማሳወቁ የሚታወስ ነው።