የኢትዮጵያ አየር መንገድ አውሮፕላን በዳላስ አይሮፕላን ማረፊያ ለማረፍ ተገደደ

(ኢሳት ዲሲ–ጥር 8/2010)

ሰኞ ረፋድ ላይ ከዋሽንግተን ዲሲ ወደ ኢትዮጵያ ይበር የነበረው የኢትዮጵያ አየር መንገድ አውሮፕላን በተፈጠረበት የቴክኒክ ችግር በዳላስ አይሮፕላን ማረፊያ ለማረፍ መገደዱ ተሰማ።

በተሳፋሪውም ሆነ በአውሮፕላኑ ሰራተኞች ላይ ምንም ጉዳት ሳይደርስ አውሮፕላኑ በሰላም ማረፉም ታውቋል።

ተሳፋሪዎቹን ሆቴል ያሳደረው የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዛሬ የአውሮፕላን ጥገናውን ጨርሶ ጉዞውን ይቀጥላል ተብሎ ይጠበቃል።

የበረራ ቁጥር 501 ቦይንግ 777-300 የሆነው የኢትዮጵያ አየር መንገድ አውሮፕላን ሰኞ ቀትር ላይ ከዋሽንግተን ዲሲ አውሮፕላን ማረፊያ ተነስቶ ጥቂት ከተጓዘ በኋላ ችግር እንደገጠመው ተመልክቷል።

ከዳላስ አውሮፕላን ማረፊያ በ50 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በሚገኘው ስታፈርድ የተባለው አካባቢ ሲደርስ በ9 ሺ ጫማ ከፍታ ላይ የነበረው የኢትዮጵያ አየር መንገድ አውሮፕላን ወዲያውኑ ከፍታውን እየቀነሰና ነዳጅ እያፈሰሰ ሲበር ታይቷል።

ይህ በቪዲዮ ጭምር የተቀረጸው ክስተት በቴክኒክ ችግር ሳቢያ የተከተለ መሆኑ የተገለጸ ሲሆን የአውሮፕላኑ ነዳጅ የፈሰሰው ሆን ተብሎ በአብራሪው እንደሆነና ይህም አውሮፕላኑ ሲያርፍ አደጋ እንዳይከተል ለመከላከል መሆኑን የበረራ ባለሙያዎች ገልጸዋል።

ከ9ሺ ጫማ እስከ 4ሺ 400 ጫማ በመውረድ በደቂቃዎች ውስጥ ወደ ተነሳበት አውሮፕላን ማረፊያ የተመለሰው የኢትዮጵያ አየር መንገድ አውሮፕላን በሰላም ማረፉም ታውቋል።

የአሜሪካ መገናኛ ብዙሃንም በክስተቱ ዙሪያ ዘገባ አቅርበዋል።

ይህ ቦይንግ 777 የበረራ ቁጥር 501 የሆነው አውሮፕላን የቴክኒክ ችግሩን መፍታት ከቻለ ዛሬ መንገደኞችን ይዞ ከዋሽንግተን ዲሲ ይነሳል ተብሎ ይጠበቃል።