ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ የ2018 ተሸላሚ ሆነ

(ኢሳት ዲሲ–ጥር 8/2010)

ታዋቂው ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ ሁለት አለም አቀፍ ተቋማት በጋራ የ2018 ተሸላሚ አድርገው መረጡት።

የሽልማት ስነስርአቱ ከነገ በስትያ በኔዘርላንድ ዘሄግ በከፍተኛ ስነስርአት የሚካሄድ መሆኑ ታውቋል።

በስነስርአቱ ላይ የከተማዋ ከንቲባ እንደሚገኙም ከወጣው መርሃ ግብር መረዳት ተችሏል።

በአለም አቀፍ ተቋማት ከፍተኛ አክብሮት እየተቸረውና ሽልማት እየተጎናጸፈ የሚገኘው ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ በአሁኑ ወቅት በቃሊቲ ወህኒ ቤት የ18 አመታት እስር ተፈርዶበት ይገኛል።

ኦክስፋም ኖቪብና ፔን ኢንተርናሽናል በጋራ ባዛጋጁት የ2018 የሽልማት ስነ ስርአት ከቬንዜላዊቷ ጸሃፊ ሚላጎርስ ስኮሮ ጋር አሸናፊ ሆኖ የተመረጠው ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ በከፍተኛ ተጽእኖና ማስፈራራት ውስጥ ለነጻነት በከፈለው ዋጋ ለሽልማት መብቃቱንም ሸላሚው አካል አስታውቋል።

የፊታችን ሀሙስ ምሽት ዘሔግ ኔዘርላንድ በሚካሄደውና ከንቲባዋ ፖሊን ክሪክ በሚታደሙበት ስነ ስርአት ለጋዜጠኛ እስክንድር ነጋና ለቬንዜላዊቷ ጸሃፊ ሚላጎርስ ስኮሮ ሽልማቱ እንደሚበረከትም ተመልክቷል።

የ18 አመታት እስራት ተፈርዶበት ባለፉት 6 አመታት በወህኒ ቤት የሚገኘው ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ መቀመጫቸውን በአሜሪካ ኒዮርክ ካደረጉት ፔን ዩ ኤስ ኤ እንዲሁም አለም አቀፉ የሰብአዊ መብት ተሟጋች ሂውማን ራይትስ ዎች እንዲሁም ከፔን ካናዳና መሰል አለም አቀፍ ተቋማት በርካታ ሽልማቶችን ማግኘቱ ታውቋል።