(ኢሳት ዲሲ–ጥር 7/2010)
የሕዝባዊ ወያኔ ሀርነት ትግራይ/ሕወሃት/ መንግስት ከእንግዲህ በማናቸውም ጥገናዊ ለውጥ ሊነሳ የማይችል ያበቃለት ቡድን መሆኑን ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ገለጹ።
አዲስአበባ ድረስ ታንክና መድፍ ይዘን የገባነው ለሁለቱ ህዝቦች ዘላቂ ጥቅም ስንል ነበር ሲሉም ተደምጠዋል።
የኤርትራው ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ትላንት በኤርትራ ቴሌቪዥን በተላለፈው ቃለ ምልልሳቸው የኢትዮጵያና የኤርትራ ህዝብ በህወሃት አደፍራሽነት 25 አመታት የገጠማቸውን ኪሳራ የሚያስመልሱበት ግዜ ሩቅ እንዳልሆነም ተናግረዋል።
በኢትዮጵያ ውስጥ የተከሰተውን ቀውስ በተመለከተ ከጋዜጠኞች ጥያቄ የቀረበላቸው ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ የወደፊቱን ለማየት ያለፈውን መቃኘት ያስፈልጋል በሚል የችግሩ መነሻ ነው ያሉትን ዘርዝረዋል።
ሕዝባዊ ወያኔ ሃርነት ትግራይ/ሕወሃት/ በኢትዮጵያ ውስጥ የበላይ ሆኖ ለመቆየት ሕዝቡን በመከፋፈል መንቀሳቀሱና አንቀጽ 39ኝን በህገ መንግስቱ ውስጥ ማካተቱ ችግር መሆኑን ገልጸዋል።
ከመነሻው ይህ መንገድ ትክክል እንዳልነበር ነግረናቸዋል ያሉት ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ከጤናማ አዕምሮ የማይመነጭ አፍራሽ ሃሳብ በግዜ ሂደት ሀገሪቱን እንዲህ ያለ ቀውስ ውስጥ እንደከተታትም አመልክተዋል።
የሀገሪቱ ኢኮኖሚ በአንድ ብሔር መያዝን ጨምሮ ለቀውሱ መባባስ ምክንያት የሆኑ ጉዳዮችን ከመነሻው እንደማያዋጣ በኤርትራ በኩል እንደተነገራቸው አስታውሰዋል።
የሕዝባዊ ወያኔ ሃርነት ትግራይ ቡድን ከእንግዲህ አብቅቶለታል ያሉት አቶ ኢሳያስ አፈወርቂ ለኢትዮጵያና ለኤርትራ ህዝብ ዘላቂ ስትራቴጂካዊ ወዳጅነት ስንል የሕወሃትን መንግስት የሚቃወሙትን መደገፋችን ትክክል ነው ብለዋል።
ቀደም ሲል ለሕወሃት የሰጡትና አዲስ አበባ ድረስ ያደረጉት ድጋፍ ለሁለቱ ህዝብ ይጠቅማል በሚል ነው ሲሉ ሁኔታውን ይገልጻሉ።
“ታንኮቻችንንና መድፎቻችንን ይዘን አዲስ አበባ ድረስ ዘልቀን የገባነው ለጉራና ለዝና ሳይሆን ለኢትዮጵያና ለኤርትራ ሕዝብ የወደፊት እድል ዋስትና ለመስጠት ነበር”ሲሉ ተናግረዋል።