ታህሳስ 08 ቀን 2004 ዓ/ም
ኢሳት ዜና:-በአምስተርዳም የኢትዮጵያ ኮሚኒቲ ባዘጋጀው የመምህር የኔሰው ገብሬ መታሰቢያ ስነስርአት ላይ የተለያዩ የፖለቲካ ድርጅቶች እና የሲቪክ ማህበረሰብ ተወካዮች ንግግር አድርገዋል።
በሆላንድ የሲቪክ ማህበራት ተወካይ የሆኑት አቶ ቦጋለ ካሳየ እንደተናገሩት የኔሰው ገብሬ ለቀረው ትውልድ ከፍተኛ የሆነ እዳ ጥሎ አልፎአል።
አቶ ቦጋለ አክለውም ” ከራሳችን ጋር በመታረቅ፣ ጭቆናን አምርረን በመጥላትና በትናንንሽ ጥቅማጥቅሞች ባለመደለል በጋራ የምንቆም ከሆነ የኔሰው ጥሎብን ያለፈውን እዳ መክፈል እንችላለን” ብለዋል።
ኢህአፓን በመወከል ንግግር ያቀረቡት አቶ ሀይሉ አበበ በበኩላቸው የኔሰው በሰራው ታሪክ ከታላላቆቹ ሰማእታት ጎን የሚያስቆመው መሆኑን ጠቅሰው፣ የየኔሰው ሞት በኢትዮጵያ ውስጥ የተንሰራፋውን የግፍ አገዛዝ፣ የመብት እጦትና አፈና እንደሚያመለክት አስረድተዋል።
የኢትዮጵያ ዲሞክራሲያዊ ሀይሎች ህብረትን በመወከል ንግግር ያደረጉት ዶ/ር አረጋዊ በርሄ ፣ ” የኔሰው በፈጸመው ገድል ከእነ አጼ ቴዎድሮስና አቡነ ጴጥሮስ የሚተናነስ አለመሆኑን ገልጠው፣ በየኔሰው ሞት የሽብረተኛው አምባገነን አገዛዝ መጋለጡን” አክለዋል።
የኔሰው በህይወቱ በከፈለው መስዋትነት ከትርምስ እንውጣ እያለን ነው ያሉት ዶ/ር አረጋዊ፣ የየኔሰውን ጥሪ ለመመለስ በሰከነ መንገድ መወያየት፣ መደጋገፍ፣ የተዘበራረቁና የሚተራመሱ ሀይሎች ቋሚ መፍትሄ መፈለግ ይኖርባቸዋል ብለዋል።
ግንቦት7 ትን በመወከል ንግግር ያደረጉት አቶ መስፍን አማን በበኩላቸው ሙስና፣ ዘረኝነት፣ አድልዋና ራስ ወዳድነት በሰፈነባት ኢትዮጵያ ፣ የኔሰው የከፈለው መስዋትነት ከፍተኛ መሆኑን ጠቅሰው፣ የየኔሰው ጥያቄ ተመለሰ የሚባለው አሁን በስልጣን ላይ ያለውን ዘረኛ መንግስት ስናስወግድ ብቻ ነው በማለት ገልጠዋል።
የቱኒዚያው አምባገነን መሪ የነበሩት ቤን አሊ ቡአዚዝ ራሱን ባቀጣለበት ጊዜ ሆስፒታል ተገኝተው ሲጎበኙት የእኛዎቹ ግን ስሙን ለማጥፋት መሽቀዳደማቸው፣ የምንታገለውን መንግስት ምን ያክል እኩይ እንደሆነ ያሳያል ብለዋል።
የየሆኑት አቶ አገሬ አዲስ እንደገለጡት ደግሞ ” የኔሰው ይህን እርምጃ የወሰደው ችግሩንና ብሶቱን የሚያወያየው ጠንካራ ድርጅት በማጣቱ መሆኑን ጠቅሰው፣ የኔሰው ተስፋ የሚጥልበት ድርጅት ቢኖር ኖሮ ምናልባትም ይህን ምርጫ ላይመርጥ ይችል እንደነበር ገልጠዋል።
ህዝቡ የኔሰውን ተከትሎ እንደ ቱኒያዚያውያን ሆ ብሎ አደባባይ ያልወጣው፣ ጠንካራ እና የሚያታግል ድርጅት በመጥፋቱ ነው ያሉት አቶ አገሬ መፍትሄውም፣ መተባባር ብቻ ነው ብለዋል።
ኢሳትን በመወከል ንግግር ያደረጉት አቶ አፈወርቅ አግደው በበኩላቸው ፣ አንድነታችን ሳይጠናከር መብታችንን ማስከበር እንዳመይቻል ተናግረው፣ የፖለቲካ ድርጅቶች ፣ የሲቪክ ማህበረሰብ አባላትና ሙያተኞች በጋራ እንዲቆሙ ጥሪ አቅርበዋል።
ዝግጅቱ የኢሳት ጋዜጠኛ የሆነችው ወ/ር ገሊላ መኮንን ለየኔሰው መታሰቢያ የሚሆን ግጥም በማቅረብ ተጠናቁዋል።