(ኢሳት ዲሲ–ታህሳስ 27/2010)
በኦሮሚያና ሶማሌ ክልል በተፈጠረው ግጭት ከ14ሺ በላይ ሕጻናት ከቤተሰቦቻቸው መለያየታቸውን ዩኒሴፍ አስታወቀ።
በሁለቱ ክልሎች በተፈጠረ ግጭት ከመኖሪያ ቀያቸው የተፈናቀሉት ደግሞ ከ84 ሺ በላይ ሕጻናት መሆናቸውን የተባበሩት መንግስታት የሕጻናት መርጃ ድርጅት ይፋ አድርጓል።
በኦሮሚያና ሶማሌ ክልሎች አዋሳኝ አካባቢዎች ያለው ግጭት ካለፈው ታህሳስ ወዲህ ለመገመት የሚያስቸግር ቀውስ መፍጠሩን የዩኒሴፍ ሪፖርት ያመለክታል።
እንደ ዩኒሴፍ ገለጻ በግጭቱ በተለይ ሕጻናትና እናቶች በከፍተኛ ሁኔታ እየተጎዱ ናቸው።
በሶማሌና ኦሮሚያ አዋሳኝ ስፍራዎች ባለው ግጭት የተነሳ 14ሺ ሕጻናት ሳይወዱ በግድ ከሚወዷቸው ቤተሰቦቻቸው ጋር ተለያይተዋል።
ከመኖሪያ ቀያቸው የተፈናቀሉት ደግሞ ከ84 ሺ በላይ ይሆናሉ።
እነዚሁም በመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ላይ መሆን የሚገባቸውና ይህው መብታቸው የተነፈጋቸው ናቸው ብሏል ዩኒሴፍ በሪፖርቱ።
ከ5 አመት በታች የሆናቸው 120 ሺ ሕጻናትና 20 ሺ የሚሆኑ ነፍሰጡር እናቶች የሚያጠቡትን ጨምሮ በምግብ እጥረት እየተሰቃዩ መሆናቸውም ነው የተገለጸው።
እናም በአንደኛ ደረጃ ትምህርት ተማሪዎችን ለማስገባት ዩኒሴፍ 2 ነጥብ 9 ሚሊየን ዶላር ያስፈልገኛል ሲልም አስታውቋል።
ለክትባት፣ለድንገተኛ ህመም መድሃኒትና ለሌሎች አስፈላጊ የጤና ቁሶች ደግሞ ተጨማሪ ሌላ 2 ነጥብ 9 ሚሊየን ዶላር አስፈላጊ መሆኑንም ገልጿል።
በኢትዮጵያ ካለፉት ሁለት አመታት ወዲህ በተነሳው ሕዝባዊ ተቃውሞ ሳቢያ አገዛዙ የሃይል ርምጃ በመውሰዱ የሕጻናት ሰቆቃ እየጨመረ መምጣቱንም ዩኒሴፍ አስታውቋል።