(ኢሳት ዲሲ–ታህሳስ 24/2010)
በተለያዩ የኦሮሚያ ክልል አካባቢዎች ህዝባዊ ተቃውሞ ሲካሄድ ዋለ።
በኢንጪኒ አደአበርጋ ህዝብ አደባባይ በመውጣት የህወሀትን ስርዓት አውግዟል።
በአዳማ ዩኒቨርስቲ 18 ተማሪዎች ተባረዋል። የቡሌ ሆራ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ግቢውን ለቀው መውጣታቸው ታውቋል።
በምስራቅ ወለጋ በገሊላ የአጋዚ ወታደሮችና ህዝቡ ፍጥጫ ውስጥ እንዳሉም የደረሰን መረጃ አመልክቷል።
በሌላ በኩል ትላንት በወልዲያ ተቀስቅሶ የነበረውን የህዝብ ተቃውሞ ተከትሎ በአካባቢው ተጨማሪ ሃይል መግባቱን ለማወቅ ተችሏል።
ዛሬ ጠዋት ምስራቅ ወለጋ ዞን ገሊላ በተሰኘች አነስተኛ ከተማ ሶስት ኦራል ወታደራዊ ተሽከርካሪዎች ገብተዋል።
የመከላከያ ሰራዊት አባላትን የጫኑት ተሽከርካሪዎቹ ለምን ዓላማ ወደ ከተማዋ እንደገቡ አልታወቀም።
ህዝቡ ተቃውሞ አንስቷል። ወደከተማዋ እንዳይዘልቁ በመደረጋቸው በአቅራቢያ ሰፍረው እንደሚገኙ የደረሰን መረጃ ያመለክታል።
በህዝቡና በሰራዊቱ መካከል ከፍተኛ ፍጥጫ የተፈጠረ መሆኑንም ለማወቅ ተችሏል።
በኢንጪኒ አደአበርጋ ዛሬ ህዝብ አደባባይ በመውጣት ተቃውሞውን አሰምቷል።
አደአበርጋ ካለፈው ሳምንት ጀምሮ ተከታታይ ተቃውሞ እየተደረገባት ሲሆን ተቃውሞ እንዲቆም ያደርጋል ብሎ አገዛዙ እምነት የጣለበት የኢህአዴግ መግለጫ ከወጣም በኋላ እምቢተኝነቱ መቀጠሉን የሚያመላክት ነው ተብሏል።
በኢንጪኒም በዛሬው ትዕይንተ ህዝብ ነዋሪው ግልብጥ ብሎ በመውጣት የህወሀት መንግስት ከስልጣን እንዲወርድ ጠይቋል።
በሌላ በኩል የፋሲል ከነማ የእግር ኳስ ቡድን አዳማ ሲገባ በተደረገው አቀባበል ከፍተኛ ሚና የተጫወቱት የአዳማ ዩኒቨርስቲ የአማራና የኦሮሞ ተማሪዎች የሚደርስባቸው ወከባ ቀጥሎ በዛሬው ዕለት 18 ተማሪዎች መባረራቸው ታውቋል።
ላለፉትሁለት ሳምንታት በዩኒቨርስቲው ቅጥር ግቢ የሰፈረው የአጋዚ ጦር በተማሪው ላይ የሚያደርሰው አፈናን ተከትሎ ተቃውሞ መነሳቱን መዘገባችን ይታወሳል።
የአማራና የኦሮሞ ተማሪዎች ተመርጠው ወከባ እየተፈጸመባቸው መሆኑን የጠቀሱት የኢሳት ምንጮች 50 ተማሪዎች ታፍነው ወዳልታወቀ ቦታ መወሰዳቸው ተገልጿል።
የዩኒቨርስቲው አስተዳደር ካለፈው ዓርብ ጀምሮ በተማሪዎች መኝታ ክፍል ፌሮ፣ ዱላ፣ ድንጋይና የሚፈነዱ ተቀጣጣይ ነገሮችን ለመስራት የሚያስችሉ መሳሪዎች እንዳይገቡ ማስታወቂያ በመለጠፍ አስጠንቅቋል።
በአዳማ ዩኒቨርስቲ በአማራና በኦሮሞ ተማሪዎች መካከል የተፈጠረው አንድነት ያሰጋው አገዛዙ ደህንነቶችን በየመኝታ ክፍሉ ማሰማራቱም ታውቋል።
በሌላ በኩል በሀገረማርያም ቡሌ ሆራ ዩኒቨርስቲ ለወራት የቆየው አለመረጋጋት ቀጥሎ ዛሬ ተማሪዎች ከግቢው መውጣታቸውን የደረሰን መረጃ ያመለክታል።
በከተማዋ የሚገኙ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ውስጥም የመማር ማስተማር ሂደቱ የተሰተጓጎለ መሆኑ ታውቋል።
በቡሌ ሆራ ዩኒቨርስቲ የገቡት የአጋዚ ሰራዊት አባላት ካልወጡ ትምህርት አንማርም ያሉት ተማሪዎች በመጨረሻም ግቢውን ለቀው መውጣታቸውን ለማወቅ ተችሏል።
ይህ በእንዲህ እንዳለም ትላንት በወልዲያ ከተማ የተካሄደውን ተቃውሞ ተከትሎ ዛሬ ከፍተኛ ቁጥር ያለው የአገዛዙ ታጣቂዎች ወደ ከተማዋ መግባታቸውን የደረሰን መረጃ አመልክቷል።
በዕለቱ ከአርባምንጭ ከነማ ጋር የእግር ኳስ ውድድር ከተካሄደ በኋላ ህዝቡ በከተማዋ ዋና ዋና ጎዳናዎች ላይ በመዘዋወር የህወሃትን መንግስት ማውገዙ የሚታወሱ ነው።
ይለያል ዘንድሮ የወያኔ ኑሮ ትላንት በወልዲያ በሰፊው የተስተጋባ የተቃውሞ መልዕክት ነው።