በኢራን 12 ሰዎች ተገደሉ

(ኢሳት ዲሲ–ታህሳስ 23/2010)

በኢራን እያሻቀበ ያለውን የኑሮ ውድነት ለመቃወምና አገዛዙን ለማውገዝ ሰልፍ በወጡ ሰዎች ላይ የጸጥታ ሃይሎች በወሰዱት ርምጃ እስካሁን 12 ሰዎች መገደላቸው ታወቀ።

ባለፈው ሳምንት መጨረሻ የጀመረው ይህ ተቃውሞ ከአውሮፓውያኑ 2009 ወዲህ የተካሄደ ትልቁ ጸረ-አገዛዝ ተቃውሞ ነው ተብሏል።

እየተባባሰ ያለውን የኑሮ ውድነትና የኢኮኖሚ ድቀት በመቃወም የተጀመረው ተቃውሞ ወደ አጠቃላይ ጸረ-መንግስት ትዕይንተ ሕዝብ እየተቀየረ መሆኑን የምዕራቡ አለም መገናኛ ብዙሃን በመዘገብ ላይ ናቸው።

የሀገሪቱ ፕሬዝዳንት ሀሰን ሮሃኒ በሳምንቱ መጨረሻ ዜጎች በሰላማዊ መንገድ የመቃወም መብታቸው የተጠበቀ ነው ብለዋል።

በጋራም የኢኮኖሚ ውድቀቱን ለመመከት እንሰራለን ሲሉ ተደምጠዋል።

ነገር ግን ፕሬዝዳንቱ ዛሬ በድጋሚ በሰጡት መግለጫ ይህ የአናሳዎች ፉከራ ነው በአብዮታችን ላይ የተቃጣ በመሆኑ ልክ እናስገባዋለን ሲሉ በመዛት የመጀመሪያውን ሃሳባቸውን ገደል ከተውታል።

በመንግስት ቁጥጥር ስር ያሉ የዜና ማሰራጫዎች የታጠቁ ተቃዋሚዎች የፖሊስ ጣቢያዎችን ለመቆጣጠር ቢሞክሩም የጸጥታ ሃይሎች ተቋቁመዋቸዋል ብለዋል።

የኢራን አብዮታዊ ዘብ የተቃውሞ ሰልፉ በዚህ የሚቀጥል ከሆነ ሰልፈኞቹ የብረት ክንድ ይቀምሳሉ ሲል ዝቷል።

በዚህ መሃል ደግሞ የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ከኢራን ጋር እያደረጉ ያለውን የቃላት ጦርነት በመቀጠል በርካታ አስተያየቶችን በቲውተር ገጻቸው ላይ አስፍረዋል።

“ለረጅም ዘመን ተጨቁኖ የኖረው የኢራን ሕዝብ አሁን የምግብም የነጻነትም ረሃብ አለበት” ብለዋል ዶናልድ ትራምፕ በቲውተር ገጻቸው።

ባለፈው ሃሙስ በኢራን ሁለተኛ ከተማ ማሻድ የተጀመረው ተቃውሞ በ2009 ከተካሄደውና “አረንጓዴ ንቅናቄ” በመባል ከሚታወቀው ተቃውሞ ወዲህ ከፍተኛው ነው ተብሏል።

የቀድሞ ፕሬዝዳንት መሐሙድ አህመዲነጃድ በአጨቃጫቂ ምርጫ ማሸነፋቸውን ተከትሎ በተደረገው ተቃውሞ 30 የሚሆኑ ሰዎች ተገድለዋል።

ወደ በስተኋላም ተቃውሞው በሃይል ርምጃ እንዲቆም ተደርጓል።

እስካሁን ወደ 400 የሚጠጉ ሰዎች በጸጥታ ሃይሎቹ ቁጥጥር ስር ሲሆኑ 200 የሚሆኑት ቅዳሜ ማታ በመዲናይቱ ቴህራን የተያዙ ናቸው።

ተቃዋሚ ሰልፈኞቹ መረጃ የሚለዋወጡባቸውን ማህበራዊ ድረገጾች መንግስት በጊዜያዊነት ያገደ መሆኑን የሀገሪቱ ቴሌቪዥን ቢያስታውቅም የኮሚኒኬሽን ሚኒስትሩ ግን በቲውተር ገጻቸው ወሬው ሀሰት ነው ሲሉ አጣጥለውታል።

በአንዳንድ የተቃውሞ ቦታዎች ሴቶች ሒጃባቸውን አውልቀው የሀገሪቱን እስላማዊ ያለባበስ ስርአት ሲጥሱ በሌሎች ቦታዎች ደግሞ የሃገሪቱ መንፈሳዊ መሪ ሃያቶላ ካሚኒ ከስልጣን እንዲወርዱ ጠይቀዋል።

ሰልፈኞቹ “ሞት ለፈላጭ ቆራጩ መሪ” “የእስላማዊ ሪፐብሊክ አንፈልግም”ሲሉ መደመጣቸውን ሲ ኤን ኤን በዘገባው አመልክቷል።