(ኢሳት ዲሲ–ታህሳስ 20/2010)
በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የተጀመረው ተቃውሞ አሁንም በተለያዩ አካባቢዎች መቀጠሉ ታወቀ።
የአርባምንጭ ዩኒቨርስቲ ተማሪዎች የትምህርት ማቆም አድማ ሲመቱ የአዳማ ዩኒቨርስቲ ተማሪዎች ደግሞ በግድ እንዲማሩ እየተደረገ መሆኑ ታውቋል።
ተቃውሞ አቅርበዋል የተባሉ 50 ተማሪዎች ተይዘው መታሰራቸውንም ምንጮች ለኢሳት ገልጸዋል።
በአርባምንጭ ዩኒቨርስቲ አባያ በተባለው ካምፓስ ውስጥ የተበተነውን የተቃውሞ ወረቀት ተከትሎ የቀጠለው አድማ ይህ ዘገባ እስከተጠናቀረበት ጊዜ ድረስ እንደቀጠለ መሆኑ ታውቋል።
በሳምንቱ መጀመሪያ ሰኞ ማለዳ በማርከር የተጻፉ ወረቀቶች አባያ ካምፓስ ውስጥ የተበተኑ ሲሆን “የኦሮሞ ደም የኛ ደም ነው፣የአማራ ደም የእኛ ደም ነው” የሚለውን ጨምሮ ወገኖቻችን እየሞቱ አንማርም የሚሉት ከተበተኑት ጽሁፎች ውስጥ ይጠቀሳሉ።
የተቆራረጡ ሰንደቅ አላማዎች አይወክሉንም የሚል ወረቀት መበተኑም ተመልክቷል።
ወረቀቱ በተበተነ በሁለተኛው ቀን የአባያ ካምፓስ አንድ ብሎክ ሕንጻ ተቃጥሏል።
ሕንጻው የተቃጠለበት ምክንያት ግን አልታወቀም።የጉዳቱ መጠንም አልተገለጸም።
በሳምንቱ መጀመሪያ የተበተነውን ወረቀትና የተከሰተውን ቃጠሎ ተከትሎ የአርባ ምንጭ ዩኒቨርስቲ ተማሪዎች አድማ ላይ መሆናቸው ታውቋል።
ከግብርና ካምፓስ ተማሪዎች በስተቀር ሁሉም በአድማ ላይ መሆናቸውን የኢሳት ምንጮች ገልጸዋል።
ይህ ዘገባ እስከተጠናቀረበት ሰአት ድረስ የጸጥታ ሃይሎች ወደ ግቢው ባይገቡም የፌደራል ፖሊስ ሃይል ጫራ በተባለ ቦታ ላይ ሰፍሮ ሁኔታውን በመከታተል ላይ መሆኑም ታውቋል።
በትግራይ አዲግራት ዩኒቨርስቲ የተከሰተን ግጭት ተከትሎ በኦሮሚያና አማራ ክልል ዩኒቨርስቲዎች የተቀጣጠለው ተቃውሞ ወደ ደቡብ ኢትዮጵያ የተዛመተው ባሳለፍንው ሳምንት ወልቂጤ ዩኒቨርስቲ ላይ በነበረው ተቃውሞ እንደሆነም መረዳት ተችሏል።
በቤንሻንጉል ጉምዝ ክልል አሶሳ ዩኒቨርስቲም ከፍተኛ ተቃውሞ መካሄዱን መዘገባችንም ይታወሳል።
ይህ በእንዲህ እንዳለም የተቃውሞ ማዕከል በሆነችው አምቦ ከተማ የሚገኘው የአምቦ ዩኒቨርስቲ ተማሪዎች ትምህርታቸውን እንዲቀጥሉ የፌደራል ፖሊስ ሃይል በማስገደድ ላይ መሆኑ ታውቋል።
የፌደራል ፖሊስ ሃይል ግቢ ውስጥ መግባቱን የገለጹት የኢሳት ምንጮች ተማሪውን እያስገደዱ ወደ ክፍል ውስጥ እያስገቡት መሆኑን መረዳት ተችሏል።
ተቃውሞ ታስተባብራላችሁ እንዲሁም የማስገደዱን ርምጃ ተቃውማችኋል የተባሉ 50 ያህል ተማሪዎችም ተይዘው ታስረዋል።
በግቢው ውስጥ አሁንም አለመረጋጋቱ እንደቀጠለ መሆኑ ታውቋል።
በሀገሪቱ ከሚገኙ 33 ያህል ዩኒቨርስቲዎች 20 በሚሆኑት ተቃውሞ መቀስቀሱንና ትምህርት መስተጓጎሉን ያመነው የሕወሃት መንግስት ትምህርት ለማስጀመር እያደረገ ያለው ጥረት መቀጠሉም ታውቋል።