(ኢሳት ዲሲ–ታህሳስ 20/2010)
በተለያዩ የኦሮሚያ ክልል አካባቢዎች ዛሬ ተቃውሞ መደረጉ ታወቀ።
በምስራቅና በምዕራብ ወለጋ በበርካታ ከተሞች በተቀሰቀሰው ተቃውሞ የአገዛዙ ሃይሎችና ነዋሪው መጋጨታቸውን ለማወቅ ተችሏል።
በባኮና አደአ በርጋ ህዝባዊ ተቃውሞ መቀስቀሱም ተሰምቷል።
በወለጋ ሻምቡ በአጋዚ ሃይል ሁለት ሰዎች ተገድለዋል።
በሌላ በኩል በሀረር መስመር ጭሮ ከተማ አቅራቢያ አራት የሰላም ባስ አውቶብሶች መሰባበራቸውን ተከትሎ በአካባቢው ውጥረት መንገሱን መረጃዎች ያመለክታሉ።
ከሀረር አዲስ አበባ መስመር የሚመላለሱ ሹፌሮች በስጋት የስራ ማቆም አድማ ሊያደርጉ እንደሚችሉም እየተነገረ ነው።
ዛሬ በተለያዩ አካባቢዎች ሕዝባዊ ንቅናቄዎች መካሄዳቸውን ለማወቅ ተችሏል።
በተለይ በምስራቅና በምዕራብ ወለጋ በርካታ አካባቢዎች ግጭት ያስከተሉ የህዝብ ተቃውሞዎች መደረጋቸውን የኢሳት ምንጮች ገልጸዋል።
በሆሮጉድሩ ሻምቡ የተነሳው ተቃውሞ የሰው ህይወት ማጥፋቱ የተገለጸ ሲሆን የአጋዚ ታጣቂዎችም ህዝቡ ላይ በቀጥታ በመተኮስ በትንሹ ሁለት ሰው ገድለዋል።
በምዕራብ ወለጋ በግምቢም ህዝባዊ ተቃውሞ የተነሳ መሆኑን መረጃዎች አመልክተዋል።
ዛሬ ጠዋት የግምቢ መሰናዶ ተማሪዎች ለታሰሩትና ለተፈናቀሉት ወገኖቻችን አጋርነታችንን እናሳያለን በሚል ባካሄዱት የተቃውሞ ትዕይንት ላይ ከአገዛዙ ታጣቂዎች ጋር ፍጥጫ ውስጥ የገቡ ቢሆንም በአባገዳዎች ሽምግልና ወደከፋ ደረጃ ሳይሻገር መቅረቱን ከአካባቢው የደረሰን መረጃ አመልክቷል።
በቄሌም ወለጋ በሺዎች የሚቆጠሩ ነዋሪዎች አደባባይ ወጥተው የአገዛዙን የግፍ ርምጃዎች ያወገዙ ሲሆን የተፈናቀሉት ወገኖች በአፋጣኝ ድጋፍ እንዲደረግላቸው ጠይቀዋል።
በደምቢዶሎና በነቀምቴ ተመሳሳይ የተቃውሞ ሰልፍ መደረጉ ታውቋል።
በምስራቅ ወለጋ ሁሉቁምባ ወረዳ ከፍተኛ የህዝብ ቁጥር የተመዘገበበት ተቃውሞ መደረጉን የጠቀሱት የመረጃ ምንጮች ህዝቡ በቁጣ ሆኖ የታሰሩት እንዲፈቱና በጨለንቆው ጭፍጨፋ የተሳተፉ ለፍርድ እንዲቀርቡ መጠየቃቸውን ገልጸዋል።
በምዕራብ ሸዋ ባኮ ከተማ ዛሬ በተካሄደው ተቃውሞ ህዝብና የአገዛዙ ታጣቂዎች መጋጨታቸውን ለማወቅ ተችሏል። የደረሰው ጉዳት ባይታወቅም በግጭቱ ወቅት የተኩስ ድምጽ ይሰማ እንደነበር ከአካባቢው ለኢሳት በደረሰው መረጃ ላይ ተመልክቷል።
በሙገር አቅራቢያ አደአ በርጋ በተሰኘች ከተማም ዛሬ ህዝባዊ ተቃውሞ መደረጉ ታውቋል።
ህዝቡ ሙሰኞች ለፍርድ ይቅረቡ ሲል በጠየቀበት በዚህ ተቃውሞ የአገዛዙ ፖሊሶች የሃይል ርምጃ በመውሰዳቸው ቁጥራቸው በውል ያልታወቁ ሰዎች መጎዳታቸው ተገልጿል።
በአርሲ ጉባ ሮቢ ከተማም ዛሬ ክፍተኛ የህዝብ ቁጥር የተመዘገበበት ተቃውሞ መደረጉ ታውቋል።
በቀድሞ መጠሪያዋ አሰበተፈሪ አሁን ጭሮ በምትባለው ከተማ አቅራቢያ አርባረከቴ ከተማ አራት የሰላም ባስ አውቶቡሶች ላይ ጥቃት መሰንዘሩንም ለማረጋገጥ ተችሏል።
ኢሳት ያነጋገራቸው አንድ የኦፌኮ የአካባቢው አመራር አባል እንደገለጹት ለቁልቢ ገብርኤል በዓል መንገደኞችን አሳፍረው የሚጓዙ የሰላም ባስ አውቶብሶችን የአካባቢው ቄሮዎች በማስቆም መንገደኞችን እንዲወርዱ ካደረጉ አውቶብሶቹን በድንጋይ በማጥቃት መስታወቶቻቸው እንዲሰባበሩ አድርገዋል።
የህወሃት ንብረት በሆነው የሰላም ባስ አውቶብስ ላይ የሚሰነዘረው ጥቃት መቀጠሉ በተመሰከረበት በዚሁ ርምጃ በተሳፋሪው ላይ ምንም ዓይነት ጉዳት አለመድረሱ ታውቋል።
በኢትዮጵያ ለተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ሰራተኞች በተበተነው የጥንቃቄ መልዕክት ላይ እንደተረጋገጠውም የሰላም ባስ አውቶብሶች ላይ ርምጃ ተወስዷል።
አካባቢው በአሁኑ ወቅት በፌደራል፣ በልዩ ሃይል፣ በመከላከያና በብረት ለበስ ተሽከርካሪዎች እየተጠበቀ ሲሆን ከሀረር አዲስ አበባ መስመር ወታደሮች በብዛት እንደሚታዩ የደረሰን መረጃ አመልክቷል።
በሀገሪቱ በተከሰተው የጸጥታ ቀውስ ምክንያት የዘንድሮ ቁልቢ ገብርዔል በዓል በተቀዛቀዘ ሁኔታ መከበሩን የጠቀሱት ምንጮች የበዓሉ ታዳሚ ቁጥርም ከወትሮው እጅግ ዝቅተኛ ነበር ብለዋል።
ከአዲስ አበባ እስከ ጅቡቲ የሚመላለሱ ሹፌሮች በየቦታው መንገድ እየተዘጋ በመሆኑ ለስራቸው ከፍተኛ ስጋት ውስጥ በመግባታቸው ስራ የማቆም አድማ ለማድረግ እንደሚችሉም እየተነገረ ነው።