(ኢሳት ዲሲ–ታህሳስ 19/2010)
በኢትዮጵያ አየር መንገድና በማላዊ አየር መንገድ መካከል የተፈጸመው የንግድ ሽርክና እርባና የሌለውና የማይጠቅም ሲሉ የሀገሪቱ መንግስት ባለስልጣናት ስምምነቱን አጣጣሉ።
የማላዊ መንግስት ባለስልጣናትና የሀገሪቱ የፓርላማ አባላት ሁለቱ አየር መንገዶች የሽርክና ስምምነት ከመረመሩ በኋላ ጉዳዩ አዋጭ እንዳልሆነ ደርሰንበታል ብለዋል።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከማላዊ አቻው ጋር ባካሄደው የንግድ ሽርክና ስምምነት 49 በመቶ ድርሻ በመያዝ የትርፍ ተከፋይ ለመሆን ነው።
የ51 በመቶ ድርሻ የሚኖረው የማላዊ አየር መንገድም ስምምነቱን ካደረገ በኋላ በሁለት አመታት ውስጥ ካለበት ኪሳራ ወጥቶ ትርፋማ ለመሆን ማለሙ ይነገራል።
ስምምነቱ ከአራት አመት በፊት ከተፈረመ በኋላ ግን የማላዊ አየር መንገድ በአገልግሎቱም ሆነ በትርፋማነቱ መሻሻል እንዳላሳየ የሀገሪቱ የሕዝብና የግል ተቋማት ትብብር ኮሚሽነር ጂሚ ሊፑንጋ ሉሳካ ታይምስ ለተባለው ጋዜጣ ገልጸዋል።
የማላዊ አየር መንገድ ከኢትዮጵያው አየር መንገድ ጋር ያደረገው የሽርክና ስምምነት ትርፋማ ቢሆን ኖሮ 20 በመቶ የሚሆነው ድርሻ ለሕዝብ አክሲዮን ለመሸጥ እቅድ እንደነበረው ዘገባው አመልክቷል።
እናም አየር መንገዱ ከኢትዮጵያ አየር መንገድ ጋር ያደረገውን ስምምነት እንዲያጤንና ውሉን እንዲሰርዝ የሀገሪቱ የፓርላማ አባላት አስጠንቅቀዋል።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ በጉዳዩ ላይ እስካሁን የሰጠው አስተያየት እንደሌለ ያገኘንው መረጃ ያመለክታል።