የአማራና የኦሮሞ ተማሪዎች ላይ የተለየ ክትትልና ወከባ እየተፈጸመ ነው

(ኢሳት ዲሲ–ታህሳስ 18/2010)

በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ አመጽ ይቀሰቀሳል በሚል ስጋት የአማራና የኦሮሞ ተማሪዎች ላይ የተለየ ክትትልና ወከባ እየተፈጸመ መሆኑ ተገለጸ።

በየመኝታ ክፍሉ ደህንነቶች እየገቡ ተማሪዎችን እንደሚያስፈራሩም የደረሰን መረጃ አመልክቷል።

ባለፈው ሰኞ ከዩኒቨርስቲው ታፍነው የተወሰዱ ተማሪዎችም የት እንደደረሱ የታወቀ ነገር የለም።

ኢሳት ያነጋገራቸው የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ተማሪዎች እንደሚሉት ባለፈው ሰኞ ታቅዶ የነበረውና የተወሰኑ ተማሪዎች መታሰራቸውን ተከትሎ በግቢው ውስጥ ብዛት ያለው ሲቪል የለበሰ ሃይል ገብቷል።

በዩኒቨርስቲው አጠገብ በሚገኘው የመናፈሻ ቦታ ባልተለመደ መልኩ የፌደራል ፖሊሶችና የታጠቁ የደህንነት ሰዎች በብዛት እንደሚታዩም ለማወቅ ተችሏል።

በግቢው ውስጥ ሶስትና አራት ሆኖ መንቀሳቀስ እንደማይቻልም ተማሪዎቹ ተናግረዋል።

ስልክ ማውራት አስቸጋሪ መሆኑንና ሲቪል በለበሱ ደህንነቶች ወከባ እንደሚፈጸምባቸው ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ ተማሪዎች ገልጸዋል።

ጥቂት ተማሪዎች ስጋት ገብቷቸው ወደቤተሰቦቻቸው የሄዱም እንዳሉ ታውቋል።

በተለይ የኦሮሞና የአማራ ተማሪዎች ላይ የሚደረገው ማዋከብ ሰሞኑን በስፋት የሚታይ መሆኑን አንድ ያነጋገርነው ተማሪ ገልጿል።

ባለፈው ሰኞ በዩኒቨርስቲው ተቃውሞ ለማድረግ ሙከራ ተደርጎ እንደነበረ የገልጹት የኢሳት ምንጮች ቁጥራቸው በውል ያልታወቁ ተማሪዎች ታፍነው መወሰዳቸው ታውቋል።

የታፈኑት ተማሪዎች ወዴት እንደተወሰዱ ለማጣራት የተደረገው ጥረትም ለጊዜው አልተሳካም።

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ አመጽ ቢቀሰቀስ ወደ ነዋሪው ይዛመታል የሚል ስጋት ያደረበት የህወሀት አገዛዝ በዩኒቨርስቲው የሚያደርገውን ጥበቃ ማጠናከሩን የደረሰን መረጃ አመልክቷል።

ሰሞኑን በአዳማ ዩኒቨርሲቲ በተነሳው ተቃውሞ የአማራና የኦሮሞ ተወላጅ የሆኑ ተማሪዎች ላይ ድብደባ መፈጸሙ የሚታወቅ ሲሆን ትላንት ስምንት ተማሪዎች መታሰራቸውን ለማወቅ ተችሏል።

ይህ በእንዲህ እንዳለም በመላ ሀገሪቱ በዩኒቨርስቲዎች የተነሳው ተቃውሞን በሃይል ለማስቆም በአገዛዙ እየተወሰደ ያለው ርምጃ እንዳልተሳካ ይነገራል።

ቢያንስ በ20 ዩኒቨርስቲዎች የመማር ማስተማር እንቅስቃሴው መስተጓጎሉን መረጃዎች ያመለክታሉ።