(ኢሳት ዲሲ –ታህሳስ 17/2010)
የህሊና እስረኞችን ለማስታወስ ነገ የበይነ መረብ ዘመቻ ሊካሄድ መሆኑ ተገለጸ።
በሀገር ቤት የሚገኙ የሰብዓዊ መብት ተቆርቋሪዎችና ጋዜጠኞች በጋራ ያዘጋጁት የበይነ መረብ ዘመቻ በተለያዩ ወህኒ ቤቶች የሚገኙ የህሊና እስረኞች ስቃይ እየተባባሰ መምጣቱን ለዓለም ዓቀፉ ማህበረሰብ ለማሳወቅ ያለመ እንደሆነ ተመልክቷል።
ለአንድ ቀን በሚደረገው በዚሁ ዘመቻ እስረኞቹ ብቻቸውን እንዳልሆኑ ለማሳየት መሆኑም ተገልጿል።
በማህበራዊ መድረኮች በፌስ ቡክና ቲውተር ዘመቻው እንደሚካሄድም ለማወቅ ተችሏል።
ዘመቻው መነሻ ያደረገው በእስረኞች ላይ የሚፈጸመው ሰቆቃ እየተባባሰ መምጣቱ እንደሆነ አዘጋጆቹ በአሰራጩት ጽሁፍ ላይ ተመልክቷል።
በፖለቲካ እምነታቸውና ሀሳባቸውን በነጻነት በመግለጻቸው ብቻ የአገዛዙ ሰለባ የሆኑት እነዚህ እስረኞች በእስር ቤት የሚደርስባቸው መጠነ ሰፊ በደልና ስቃይ መስዋዕትነትን በሚከፍሉለት ህዝብ ዘንድ ይበልጥ እንዲታወቅ ማድረግ አስፈላጊ ሆኖ መገኘቱ ተጠቅሷል።
የዘመቻው አዘጋጆች እንዳሉት እስረኞች እንዲፈቱ፣ የሚፈፀምባቸው በደል እንዲቆም፣ ይሰሙ የነበሩ ድምጾች እንዳይጠፉ ማድረግ የዘመቻው አንዱ አካል ነው።
አገዛዙ የአፈና ጡንቻውን ይበልጥ በማሳረፍ የህሊና እስረኞችን ጠባብ በሆነ ጨለማ ክፍል ውስጥ እንዲሰቃዩ ማደረጉን አጠናክሮ ገፍቶበታል።
ስለእነዚህ እስረኞች እየተከታተለ በደላቸውን የሚናገር አካል የለም።
የሚደርስባቸውን በደል በማስረጃ አጠናቅሮ ግፍ የሚፈጽሙትን ለይቶ ለፍትህ ለማቅረብ የሚደረግ ጥረት አይታይም ያለው የአዘጋጆቹ መግለጫ እነዚህን ወገኖች ለማስታወስ በደላቸውን ለዓለም ዓቀፉ ማህበረሰብ እንዲያውቀው ለማድረግ የአንድ ቀን ዘመቻ መከፈቱን ገልጿል።
ዘመቻው ነገ ታህሳስ 18 2010 የሚካሄድ ነው ተብሏል።
ዓላማውም የፖለቲካ እና የሕሊና እስረኞችን ለአንድ ቀን ማስታወስና ፍትሕ እንዲሰጣቸው መወትወት እንደሆነ ተመልክቷል።
እያንዳንዱ ተሳታፊ ስለሚያውቀው አንድ የህሊና ወይም የፖለቲካ እስረኛ በመጻፍ፣ ለዘመቻው የተዘጋጀውን የፕሮፋይል ምስል በመጠቀም፣ የግፍ እስረኞችን ጉዳይ ለአደባባይ በማብቃት፣ ቤተሰባቸውንና እነርሱን በመጠየቅና በመርዳት እንዲሁም እስረኞቹ እንዳልተዘነጉና እንደማይዘነጉ ቃል በመግባት ዘመቻው የሚከናወን መሆኑ ታውቋል።
የዘመቻው አፈጻጸም በዝርዝር የተቀመጠ ሲሆን በየትኛውም እስር ቤት ጨለማ ቤት ውስጥ የሚገኙና ኢሰብአዊ ድርጊት የተፈፀመባቸውን እስረኞች ማስታወስ፣ በየእስር ቤቱ ህክምና የተከለከሉትን ማስታወስና ህክምና እንዲያገኙ መጠየቅ፣ ህክምና ተከልክለውና ተደብድበው ለሞት የተዳረጉትን ማስታወስ፣ ከህግ ውጭ በጠበቆቻቸው፣ በቤተሰቦቻቸው፣ በሀይማኖት አባትና በሌሎችም እንዳይጠየቁ የተከለከሉትን ማስታወስና መብታቸው እንዲከበር መጠየቅ፣ በአሁኑ ወቅት በየእስር ቤቱ የሚገኙት የፖለቲካ እስረኞች በመሆናቸው እንዲፈቱ በተገኘው አጋጣሚ ሁሉ ጫና ማድረግ፣በነገው ዘመቻ የሚከናወኑ ተግባራት እንደሆኑም ተገልጿል።