የፈረንጆቹ ገና ተከበረ

(ኢሳት ዲሲ–ታህሳስ 16/2010)

የፈረንጆቹ የገና በአል በበርካታ የአለም ክፍሎች በደማቅ ስነስርአት ተከብሮ ዋለ።

የካቶሊኩ ሊቀ ጳጳስ ፓፕ ፍራንሲስ በበአሉ ዋዜማ ባስተላለፉት መልዕክት አለም ስደተኞችን እንድታስተናግድ የክርስትና እምነት ግድ ይላል ብለዋል።

ኢየሱስ ክርስቶስ በተወለደበት ቤተልሄም እየተካሄደ ያለው ግጭት በአሉን ጥላ ያጠላበት መሆኑንም መረጃዎች አመልክተዋል።

የካቶሊኩ ሊቀ ጳጳስ ፍራንሲስ ትላንት በዋዜማው በፈረንጆቹ ገና ዋዜማ ባስተላለፉት መልዕክታቸው በአውሮፓ ለአክራሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች ያለው ድጋፍ እየጨመረ መምጣቱን ተናግረዋል።

የክርስትና እምነት ግን ስደተኞችን እንድንቀበል ያስገድደናል ብለዋል።

ማርያምና ዮሴፍ ስደተኞች ነበሩ።–በቤተልሄም ጥላ ከለላ ለማግኘት ብዙ ተንገላተዋል ብለዋል ጳጳሱ።

በአርጀንቲና ከጣሊያን ከተሰደዱ ቤተሰቦች የተወለዱት ፍራንሲስ በስደተኞች መብት ጉዳይ ላይ ጠንከር ያለ አቋም አላቸው።

በዚህ አመት ብቻ 160ሺ የሚሆኑ አፍሪካውያን ስደተኞች በሜዲትራኒያን ባህር ተሻግረው አውሮፓ ለመግባት ለሕይወት እጅግ አደገኛ ጉዞ አድርገዋል።

ከነዚህ 3ሺ የሚሆኑት ደግሞ የባህር ሲሳይ ሆነዋል ይላል የተባበሩት መንግስታት ሪፖርት።

በቤተልሄም የነበረው የገና ስነስርአት ግን የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ኢየሩሳሌም የእስራኤል መዲና ነች ብለው ከሁለት ሳምንት በፊት እውቅና ከሰጡ በኋላ በተነሳው ብጥብጥ ምክንያት ቀዝቀዝ ባለ ሁኔታ ነበር የተከበረው።

ካለፉት አመታት በአል ጋር ሲነጻጸር በቤተልሔም ዝቅተኛ ቁጥር ያለው ታዳሚ ነበር የተገኘው ።

በፍልስጤማውያንና በእስራኤል ሃይሎች መካከል እየተካሄደ ያለው ግጭትም ጎብኝዎች ወደ ስፍራው እንዲመጡ የሚጋብዝ ባለመሆኑ ለጎብኝዎቹ ቁጥር መቀነስ ምክንያት ሆኗል።

ክሌር ደጎ የተባለችና ከፈረንሳይ የመጣች ጎብኚ ስትናገር ፍልስጤማውያንና የተቀረውን አለም ያስቆጣው የፕሬዝዳንት ትራምፕ ውሳኔ በዚች በተቀደሰች ስፍራ መጥቼ በአሉን ከማክበር አላገደኝም ብላለች።

የአንድ ሰው አስተያየት የቅድስቲቱን ስፍራ ማወክ የለበትም።

ትራምፕ ምንም አሉ ምን ኢየሩሳሌም የሁሉም ነች።

ወደፊትም የሁሉም ሆና ትቀጥላለች ብለዋል ክሌር።

በሕንድ 24 ሚሊየን ወይንም 2 ብመቶ የሚሆኑ ክርስቲያኖች በአሉን አክብረዋል።

የቀኝ ክንፍ የሂንዱ እምነት አራማጅ ቡድን ግን በአሉ በትምህርት ቤቶች እንዳይከበር ማስጠንቀቂያ ሰጥቶ ነበር።

በዚህም ምክንያት ይመስላል የገናን መዝሙር ሲዘምሩ የነበሩ ልጆች በፖሊስ ተይዘው መኪናቸው እንዲቃጠል ተደርጓል።