መንግስት ችግሮችን በድርድርና በውይይት እንዲፈታ ተጠየቀ

(ኢሳት ዲሲ–ታህሳስ 16/2010)

በኢትዮጵያ የተከሰቱ ችግሮችን መንግስት በድርድርና በውይይት እንዲፈታ የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ጥሪ አቀረበች።

አገሪቱን ከውድቀት፣ ሕዝቡንም ከሞትና ከስደት ለመታደግ መንግስት ከባድ ሞራላዊና መንግስታዊ ሃላፊነት እንዳለበትም አሳስባለች።

የሃይማኖት አባቶችም አጥፊውን ወገን ያለፍርሃት እንዲገስጹም ጥሪዋን አቅርባለች።

የኢትዮጵያ ወቅታዊ ሁኔታ እንዳሳሰባት የገለጸችው የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን በ34ኛው የጳጳሳት መደበኛ ጉባኤ በጉዳዩ ላይ ከመከረች በኋላ መግለጫ ማውጣቷ ተመልክቷል።

የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን በብጹዕ ካርዲናል አቡነ ብርሃነ ኢየሱስ አማካኝነት ሐሙስ ታህሳስ 12/2010 ይፋ ባደረገችው በዚህ መግለጫ 2009 ለኢትዮጵያ ፈታኝ ጊዜ እንደነበር አስታውቃለች።

ዘንድሮም ይህ ሁኔታ በመቀጠሉ የማህበረሰቡ አብሮነትና አንድነት አደጋ ላይ ወድቋል ስትልም ሁኔታውን ገምግማለች።

በኦሮሚያና በኢትዮጵያ ሶማሌ ክልልሎች እንዲሁም በሌሎች አካባቢዎች በተነሱት ግጭቶች ላለቁት ወገኖች ሐዘኑን በመግለጽ የመንግስት አካላት ማናቸውንም ልዩነት ወደ ጎን በመተው ሕዝብንና አገርን ለማዳን ግንባር ቀደም ሚና እንዲጫወቱም ጥሪዋን አቅርባለች።

ማንኛውንም ልዩነት በድርድርና በውይይት በመፍታት ሐገሪቱን ከውድቀት ሕዝቡን ደግሞ ከመከራና ከስደት የመታደግ ሃላፊነት በመንግስት ላይ መውደቁን አሳስባለች።

ከብሔርተኝነት ጋር በተያያዙ እየተከተሉት ላሉት ግጭቶች፣ በዚህም ለሚከተለው ሞትና መፈናቀል ትኩረት እንዲሰጠውና መፍትሔም እንዲፈለግለት የጠየቀችው የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት እንዲሁም በስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራ እየተከሰቱ ያሉ ግጭቶች እንዳሳሰቧትም ገልጻለች። ለዚህም መፍትሄ እንዲበጅለት ጥሪዋን አቅርባለች።

ለሃይማኖት አባቶችም በቀረበው ጥሪ በአካባቢያቸውም ሆነ በአገር አቀፍ ደረጃ ድምጻቸውን ከፍ አድርገው በማሰማት የህግ የበላይነት እንዲሰፍንና የሰው ልጆች መብት እንዲከበር አጥፊዎችን ያለፍርሃት እንዲገስጹም ጠይቃለች።

ዕውነትን መሰረት ያደረገ ዕርቀ ሰላም እንዲወርድም ሃላፊነታቸውን እንዲወጡ ጥሪዋን አቅርባለች።