በሀገሪቱ ያለው ችግር የብሔር ፖለቲካ ያመጣው መዘዝ ነው ተባለ

(ኢሳት ዲሲ–ታህሳስ 16/2010)

የኢትዮጵያ ወቅታዊ ሁኔታ ያሳሰባቸው ታዋቂ ዜጎች በሀገሪቱ ያለው ችግር የብሔር ፖለቲካ ያመጣው መዘዝ መሆኑን ገለጹ።

በወቅታዊ የፖለቲካ ሁኔታ ላይ አስተያየታቸውን የሰጡት ዜጎች በአሁኑ ጊዜ የሰው ሕይወትና ንብረት እየወደመ እንዲመጣ ምክንያት የሆነው ልዩነትን የሚያበረታታው ሕገመንግስት ነው ብለዋል።

ከፊሎቹ ይህን ሀሳብ ቢቃወሙም ብዙዎቹ ግን የብሔር ፖለቲካው ያመጣውን መዘዝ ለማስወገድ ሕዝቡ ለአንድነቱ መቆም አለበት ብለዋል።

ሕዝባዊና ሀገራዊ እርቅ እንዲደረግ ጥሪ ያቀረቡም አሉ።

በኢትዮጵያ ሁኔታ ታዋቂ ሰዎችና ዜጎች አስተያየት እንዲሰጡ ሀገር ውስጥ ባለ ጋዜጣ ተጋብዘው ነበር።

የኢትዮጵያ የወቅቱ ፖለቲካዊ ሁኔታ በእጅጉ ያሳሰባቸው እነዚሁ ዜጎች ታዲያ በጥቅሉ ሁኔታው አስጊ እንደሆነና የሰው ሕይወትና ንብረት እየወደመ መሆኑ አስጨንቆናል ብለዋል።

በችግሩ አሳሳቢነት ላይ ሁሉም ተመሳሳይ ሀሳብ ቢኖራቸውም በመፍትሄው ላይ ግን ሀሳባቸው የተቃረነም ነበሩ።

ታዋቂው የንግድ ሰው አቶ ኢየሱስወርቅ ዛፉ ችግሩ ሲብላላ የነበረ የሕዝብ ብሶት ነው ይላሉ።

በኢትዮጵያ አሁን ለተከሰተው ውጥረትና የሰላም እጦት ጸሃፊ ተውኔት አያልነህ ሙላት ደግሞ የችግሩ ዋናው ምክንያት ሕገመንግስቱ መሆኑን ይናገራል።

እንደ አቶ አያልነህ ገለጻ ሕገመንግስቱ ለኢትዮጵያዊነት ቦታ የማይሰጥ መሆኑ ሁሉ ነገር በብሔር ስሜት የሚታዘዝና የሚነድ እንዲሆን አድርጎታል።

አቶ ጸጋ አስማረ የተባሉ የነዳጅ ማመላለሻ ትራንስፖርት ባለንብረቶች ማህበር ምክትል ፕሬዝዳንትም በዚሁ ሃሳብ ይስማማሉ።

እንደ እሳቸው አባባል አሁን በኢትዮጵያ ለተንሰራፋው ችግር ዋነኛ መንስኤ የዘር ፖለቲካው ነው።

የፊልም ባለሙያው ያሬድ ሹመቴ እንደሚለው ደግሞ የኢትዮጵያን ሕዝብ ሕዝቦች ብሎ የፈረጀው ሕገ መንግስት እንደ አንድ ሕዝብ በአንድነት ይኖር የነበረውን ሕብረተሰብ በእጅጉ ለያይቶታል።

እናም ለአንድነት ቅድሚያ የማይሰጠው ሕገመንግስት ሀገሪቱን የከፋ ችግር ውስጥ ከቷታል ብሏል።

ዶክተር አግደው ረዴ የተባለው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን የልማትና ክርስቲያናዊ ተራድኦ ኪሚሽን ኮሚሽነር ደግሞ አሁን ለተፈጠረው ችግር መንስኤው አሁን በሀገሪቱ የተፈጠረው እድገት ነው ባይ ናቸው።

ዕድገት ያለ ግጭት ስለማይሆን ችግሩ ተፈጥሯል ብለዋል።

አቶ ኢየሱስወርቅ ዛፉ በሀገሪቱ ለተፈጠረው ለዚህ ችግር መፍትሄው ሕዝባዊና ሀገራዊ እርቅ ማካሄድ ነው ይላሉ።

እናም ሀገሪቱ ከገባችበት ችግር ለማውጣት የጥምረት ወይም የሕብረት መንግስት መፍጠር ያስፈልጋል ነው ያሉት።

አቶ አያልነህ ሙላት ደግሞ መፍትሄው ያለው ሕዝቡ ዘንድ ነው ብቻ ነው ይላል።

መንግስት የችግሩ ፈጣሪ ስለሆነ የራሱን ችግር ራሱ ይፈታል ብዬ አላምንም ሲሉም አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።

የፊልም ባለሙያው ያሬድ ሹመቴ በበኩሉ አሁን የጠፋው ጥፋት 27 አመት በወሰደ የብሔር ፖለቲካ ምክንያት የመጣ በመሆኑ ረዘም ላለ ጊዜ ስለ አንድነትና ህብረት መሰበክ አለበት ብሏል።