በኦሮሚያ ተቃውሞው እንደቀጠለ ነው  

(ኢሳት ዲሲ–ታሕሳስ 12/2010) በኦሮሚያ ክልል በተለያዩ ከተሞች ተቃውሞ ሲደረግ መዋሉ ታወቀ።

በሀረርጌ የአጋዚ ወታደሮች መገደላቸውን የደረሰን መረጃ አመልክቷል።

በመቱ ለአራተኛ ቀን ተቃውሞው የቀጠለ ሲሆን በጂማና በቄሌም ወለጋም ተመሳሳይ የተቃውሞ ትዕይንት መደረጉን ለማወቅ ተችሏል።

በወለጋ በአንዳንድ ቦታዎች ትምህርት ቤቶች ተዘግተዋል።

የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረስ አባላትና ደጋፊዎች የትምህርት አገልግሎትን ጨምሮ ብድርና እርዳታ እንደተከለከሉ ተገልጿል።

ህዝባዊ ተቃውሞና ግድያ ተለይቶት በማያውቀው ሀረርጌ ዛሬም ጠንከር ያለ የህዝብ አመጽ መካሄዱን መረጃዎች አመልክተዋል።

በሀበሩ ዋጩቲ ከተማ የተነሳውን የህዝብ ንቅናቄ በሃይል ለማስቆም ከተሰማሩ የአጋዚ ወታደሮች መሃል በትንሹ ሁለቱ መገደላቸውን ለማወቅ ተችሏል።

አንዳንድ መረጃዎች የተገደሉትን የአጋዚ ወታደሮች ቁጥር አራት እንደሆኑ ቢያመላክቱም ማረጋገጥ የተቻለው የሁለቱን ብቻ ነው።

በአጸፋው የአጋዚ ሃይል በወሰደው ርምጃም በርካታ ሰዎች መጎዳታቸው ታውቋል።

ዛሬ በመቱ ለአራተኛ ቀን የቀጠለ ተቃውሞ መካሄዱም ታውቋል።

በዛሬው ተቃውሞ በተለየ ሁኔታ ከ300 በላይ ሴት ተማሪዎች ለብቻቸው አደባባይ በመውጣት አዲሱ የትምህርት ሚኒስቴር የመግቢያ ፈተና እንዲቀር በመጠየቅ ሰልፍ አድርገዋል።

በተያያዘም የጦር መሳሪያዎችና የቅስቀሳ ጽሁፎች በቤታቸው በመገኘቱ በኦሮሚያ ክልል ፖሊስ ተይዘው ጉዳያቸው በፍርድ ቤት እየታየላቸው የሚገኙት ሁለቱ የህወሃት አባላት ዛሬ በነበራቸው ቀጠሮ ላይ ህዝቡ ፍርድ ቤት በመሄድ አጋጣሚውን ተጠቅሞ በስርዓቱ ላይ ተቃውሞ ማሰማቱን የደረሰን መረጃ አመልክቷል።

በመቱ ለአራተኛ ቀን የቀጠለው ተቃውሞ በጨለንቆ በመከላከያ ሰራዊት የተፈጸመውን ጭፍጨፋ በማውገዝ የሚካሄድ ሲሆን በሀዘን የታጀበው እንቅስቃሴ ልዩ ትኩረት አግኝቷል።

በመቱ የአጋዚ ሰራዊት በአስቸኳይ አካባቢውን ለቆ እንዲወጣ መጠየቁንም የደረሰን መረጃ ላይ ተመልክቷል።

በወለጋ በቄሌም ወለጋ፣ በነጆ፣ በደምቢዶሎ፣ በቤጊና በሌሎች የገጠር መንደሮች ተቃውሞ መካሄዱን ከደረሰን መረጃ ለማወቅ ተችሏል።

በቄሌም ወለጋ ቁጥሩ ከፍተኛ የሆነ ህዝብ አደባባይ በመውጣት የህወሀት ስርዓትን ያወገዘ ሲሆን በንጹሃን ግድያ እጃቸው ያለበት ባለስልጣናትና ታጣቂዎች ለፍርድ እንዲቀርቡ ጠይቀዋል።

ከዚሁ ጋር በተያያዘ በወለጋ የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረስ አባላትና ደጋፊዎች ጥቃት እየደረሰባቸው እንደሆነ የቀጠናው የድርጅቱ ተወካይ ለኢሳት ገልጸዋል።

አባላቱና ደጋፊዎቹ ብድር ይከለከላሉ። እርዳታ ይነፈጋቸዋል። የትምህርት ዕድል እንዳያገኙ ይደረጋል ብለዋል ተወካዩ።

እዚያው ወለጋ ውስጥ በአንዳንድ ወረዳዎች ውስጥ ትምህርት ቤቶች መዘጋታቸው ታውቋል። በነቀምት የማስተማር ሂደቱ እየተስተጓጎለም እንደሆነ ተገልጿል።

በጂማ የጨለንቆውን ጭፍጨፋ የሚያወግዝና ለተገደሉት ሀዘን የተገለጸበት ትዕይንት ተካሂዷል።

ጥቁር ልብስ የለበሱ ወጣቶች ሀዘናቸውን በመግለጽ አደባባይ ወጥተዋል። በሻሸመኔ አካባቢም የተቃውሞ ሰልፍ መደረጉን ለማወቅ ተችሏል።

በሌላ በኩል ባለፈው ሰኞ በተካሄደውና እስከትላንት ድረስ በዘለቀው የድሬዳዋ ዩኒቨርስቲ ተቃውሞ ምክንያት ትምህርት ከቆመ አራተኛ ቀኑን ይዟል።

በተቃውሞ የተጎዱ በርካታ ተማሪዎች ህክምና ማዕከላት የሚገኙ ሲሆን ለጊዜው ቁጥራቸው የማይታወቁ ተማሪዎች መታሰራቸው ታውቋል።