(ኢሳት ዲሲ–ታህሳስ 10/2010)
በ8 ጉዳዮች በሽብር ወንጀል በእንግሊዝ መንግስት የተከሰሱት ታዋቂው ምሁርና ፖለቲከኛ ዶክተር ታደሰ ብሩ በተከሰሱባቸው ሁሉም ጉዳዮች ነጻ ተባሉ።
ጉዳዩን ሲከታተል የነበረው የሀገሪቱ ፍርድ ቤት በሕዝብ በተመረጠ ዳኝነት/ጁሪ/ ዶክተር ታደሰ ብሩን በሙሉ ድምጽ ነጻ ናቸው ብሏል።
ዶክተር ታደሰ ብሩ ሂደቱን ሲከታተሉና ሲጨነቁ ለነበሩ ኢትዮጵያውያን ምስጋና አቅርበዋል።
ዶክተር ታደሰ ብሩ የተከሰሱት የሽብር ወንጀሎች ለምርምርና ለነጻነት ትግል የተጠቀሙባቸው የኤሌክትሮኒክስ መጻሕፍትን ይዘህ ተገኝተሃል የሚልና በሽብር ማሰልጠኛ ቦታዎች ተገኝተሃል በሚል ነበር።
ጉዳዮቹ በክስ መልክ በእንግሊዝ አቃቢ ሕግ ቢቀርቡም በሀገሪቱ የፍትህ ስርአት ያለ በመሆኑ ሁኔታው ተጣርቶ ነጻ እንደሚሆኑ ብዙዎች ገምተው ነበር።
እንደተገመተው በሕዝብ በተመረጡ ዳኞች/ጁሪ/ሲታይ የነበረው የዶክተር ታደሰ ብሩ ክስ በ8ቱም ጉዳዮች ነጻ ተብሎ ውሳኔ አግኝቷል።
ዶክተር ታደሰ ብሩ ከውሳኔው በኋላ ለኢሳት እንደገለጹት በክሱ የቀረቡ 8ቱም ጉዳዮች ትክክል እንዳልነበሩ በመጨረሻ ተረጋግጧል።
ዶክተር ታደሰ ብሩ እስካሁን በነበረው የክስ ሂደት ጉዳዩ አሳስቧቸው ሲጨነቁ ለነበሩ ኢትዮጵያውያንም ምስጋና አቅርበዋል።
የዶክተር ታደሰ ብሩን በሽብር ወንጀል መጠርጠር መነሻ በማድረግ በሕወሃት የሚደገፉ የሀገር ውስጥ መገናኛ ብዙሃን ጉዳዩን ሲያራግቡ እንደነበር ይታወሳል።