(ኢሳት ዲሲ–ታህሳስ 9/2010)
በኢትዮጵያ ያለው ቀውስና ግጭት አሳሳቢ ደረጃ ላይ መድረሱን አንድ ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ የኢሕአዴግ ባለስልጣን መግለጻቸው ተነገረ።
በጨለንቆ በቅርቡ የተፈጸመውን ጅምላ ግድያ ለማውገዝ በአምቦ ከተማ በተካሄደ ተቃውሞ በመከላከያ ሰራዊትና በኦሮሚያ ፖሊስ መካከል በተደረገው የተኩስ ልውውጥ የሞቱና የቆሰሉ እንደነበሩም ለማወቅ ተችሏል።
እዚህ ደረጃ የደረሰው የሀገሪቱ ቀውስና ግጭት አሳሳቢ እየሆነ የመጣውም በኢትዮጵያ ያለውን የጸጥታ ችግር ለመፍታት ብሔራዊ የደህንነት ምክር ቤቱ በቅርቡ ያወጣው እቅድ ተግባራዊ ባለመሆኑና በመክሸፉ ነው ሲሉ ባልስልጣኑ መግለጻቸውን ሪፖርተር ጋዜጣ ዘግቧል።
የመከላከያ፣የደህንነትና ልዩ ልዩ የጸጥታ አካላትን በማካተት በቅርቡ የተካሄደው የብሔራዊ ደህንነት ምክር ቤት በሀገሪቱ ያለውን ቀውስና ግጭት ለመፍታት የአንድ አመት እቅድ አውጥቶ ነበር።
ይህም እቅድ ከአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ባልተናነሰ ሰዎችን ለማሰርና ርምጃ ለመውሰድ ስልጣን የሚሰጥ መዋቅር እስከመዘርጋት ያስቻለ ነው።
ይህም ሆኖ ግን የሕዝቡ ተቃውሞ እያየለ በመምጣቱ ይህ እቅድ ከወጣም በኋላ ቢሆን በስፖርት ማዘውተሪያ ቦታዎች፣በዩኒቨርስቲዎችና በልዩ ልዩ ከተሞች ግጭቶችና የሰዎች መገደል ተከስቷል።
እናም ይህ ሁኔታ ያበሳጫቸው አንድ ስማቸው እንዲገለጽ ያልፈለጉ የኢሕአዴግ ባለስልጣን የብሔራዊ ደህንነት ምክር ቤቱ እቅድ ባለመተግበሩ ችግሩ ደርሷል ብለዋል።
እንደ ኢሕአዴግ ባለስልጣኑ ገለጻ የፖለቲካ መፍትሄው ባለመቅደሙ የብሔራዊ ምክር ቤቱ እቅድ ሙሉ በሙሉ ሊተገበር አልቻለም።
በዚህም የተነሳ ብሔር ተኮር ግጭት እየተዛመተ ወደ አሳሳቢነት ደረጃ ደርሷል ነው ያሉት።
እንደ አብነትም በጨለንቆ የተፈጸመውን ጅምላ ግድያ ተከትሎ በአምቦ ከተማ ተቃውሞ ሲካሄድ በመከላከያና በኦሮሚያ ፖሊስ መካከል የተኩስ ልውውጥ እንደነበርም ነው የተዘገበው።
የተኩስ ልውውጡ ምክንያት ደግሞ የኦሮሚያ ፖሊስ ሕዝቡ የሚያካሂደው ተቃውሞ ሰላማዊ ስለሆነ የሃይል ርምጃ መውሰድ አያስፈልግም በማለቱ ነው ተብሏል።
በሁለቱም ወገኖች በተካሄደው የተኩስ ልውውጥም የሞቱና የቆሰሉ እንደነበሩም ነው የተገለጸው።
በኢትዮጵያ ያለውን ግጭትና ቀውስ መነሻ በማድረግ የኢሕአዴግ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ስብሰባ በዝግ እየተካሄደ ይገኛል።
የስብሰባው ውጤት ባይገለጽም በአራቱ የኢሕአዴግ አባል ድርጅቶች መካከል ጭቅጭቅና ንትርኩ መቀጠሉ ይነገራል።