(ኢሳት ዲሲ–ታህሳስ 6/2010)
የሩዋንዳ መንግስት በሀገሪቱ ሺሻ እንዳይሸጥ እገዳ ጣለ።
የሀገሪቱ የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር እንዳስታወቀው እገዳው የተጣለው የአለም አቀፉን የጤና ድርጅት ምክር በመከተል ነው።
ሩዋንዳ ሺሻን በማገድ በአፍሪካ ሁለተኛ ሀገር ሆናለች።
ባለፈው አመት ሀምሌ ታንዛኒያ ሺሻን ማገዷ ይታወቃል።
አለም አቀፉ የጤና ድርጅት WHO ሺሻ ለጤና እጅግ አደገኛና ጠንካራ ሱስ የሚያሲዝ ነው በሚል ሀገራት እገዳና ቁጥጥር እንዲያደርጉ በመወትወት ላይ ይገኛል።
ሩዋንዳ ሺሻን የማገዷ ዜና ከተሰማ በኋላ በሌሎች የአፍሪካ ሀገራት የሚኖሩ ሰዎች ጭምር አስተያየትና ትችት በመሰንዘር ላይ ናቸው።
አንዳንዶች እገዳው የተጣለው የሲጋራ ነጋዴ ድርጅቶችን ጥቅም ለመጠበቅ ነው ሲሉ ሌሎች ደግሞ የሲጋራም አደገኝነት እየታወቀ ሺሻን ለይቶ ማገዱ ትርጉም የማይሰጥ ነው ብለዋል።
የአለም የጤና ድርጅት ምክር እንደሚለው በአንድ ሰአት ውስጥ የሚጨሰው የሺሻ መጠን ቢያንስ 100 ሲጋራን የማጨስ ያህል ነው።
በዚህም ምክንያት ይመስላል አንዳንድ አስተያየት ሰጪዎች 100 ሲጋራ ማጨስ የሚፈቀድ ከሆነ ሺሻን ለአንድ ሰአት ማጨስ ለምን ይከለከላል ሲሉ የሚጠይቁት።
የኬንያ መንግስት ሺሻን ቢያግድ 3 ሚሊየን የሚሆኑ ቆነጃጅትን ቁጣ ይጋብዛል ብሏል አንድ ኬንያዊ በትዊተር ላይ ባሰፈረው አስተያየት።
ሺሻ አደገኛ የሆኑ እንደ ካርበን ሞኖክሳይድ፣ታር ወይም ጥቀርሻ መሰል ፈሳሽ እንዲሁም መርዛማ የሆኑ አርሰኒክና ሌድ የተባሉ ብረቶችን ይዟል።
ከዚህ በተጨማሪ ደግሞ ሱስ አስያዡን ኒኮቲን በብዛት አጭቋል።
በዚህ መሰረት ደግሞ ሺሻ አብዛኛውን በሲጋራ ውስጥ የሚገኙ አደገኛ ነገሮችን ይዟል ማለት ነው።
ሺሻ ለካንሰር፣ለልብና ለሳምባ ሕመም እንዲሁም ለተለያዩ ገዳይ በሽታዎች እንደሚያጋልጥም ሳይንስ ያስጠነቅቃል።
በጎረቤት ኬንያ ሺሻ ሙሉ በሙሉ ባይታገድም የሀገሪቱ የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር 19 የሚሆኑ የሺሻ ፍሌቨርስ ወይም ጣዕሞችን አግዷል።
ምክንያቱ ደግሞ አንዳንዶቹ ጣዕሞች የሔሮይን፣ኮኬይንና ሞርፊን ንጥረ ነገሮችን በመያዛቸው ነው።
ሺሻ በአፍሪካ፣በአረቡ አለም እንዲሁም በአሜሪካ በፍጥነት እየተስፋፋ መጥቷል።
ለጊዜው ያገዱት ሀገራት ግን ሩዋንዳ፣ሳውዳረቢያ፣ዮርዳኖስ፣ፓኪስታንና ታንዛኒያ ናቸው።
ሺሻ በብዙ ኢትዮጵያውያን ወጣቶች ዘንድ ዋና የመዝናኛና የጊዜ ማሳለፊያ እየሆነ ከመጣ ሰነባብቷል።
የጤና ባለሙያዎች ግን ጭሱ የሚያስከትለውን የጤናና የማህበራዊ ቀውስ በመጠቆም ልምዱ እንዲቀር ይመክራሉ።