(ኢሳት ዜና–ሕዳር 28/2010)
የዋልድባው መነኩሴ አባ ገብረኢየሱስ ዛሬ ለሊቱን በእስር ቤት ሲደበደቡ አድረው ወደ ጭለማ ቤት መወርወራቸው ተሰማ።
በሽብር ወንጀል ተከሶ ያለምንም ብይን በጭለማ ቤት ታስሮ የሚገኘው አስቻለው ደሴ አባ ገብረየሱስ ስብርብር እንዲሉ ተደርገው ከተደበደቡ በኋላ በሱ ጭለማ ክፍል መጣላቸውን መስክሯል።
የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 4ኛ ወንጀል ችሎት የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ስልጣኑን አቷል ሲል ብይን መስጠቱም ተሰምቷል።
በእነ አስቻለው የክስ መዝገብ አንደኛ ተከሳሽ አስቻለው ደሴ በሕዳር 14/2010 በዋለው ችሎት ፊት ቀርቦ ልብሱን በአደባባይ በማውለቅ በእስር ቤት እንዳኮላሹትና ከባድ ስቃይ እየደረሰበ መሆኑን የፍትህ ያለ ሲል በአደባባይ መናገሩ ይታወሳል።
አሁን ላይ ህይወቴ አስጊ ሁኔታ ላይ ወድቋ ሲል የተናገረው አስቻለው የኔ አላግባብ መሰቃየ ሲገርመኝ ዛሬ ለሊት ደግሞ የዋልድባውን መነኩሴ አባ ገብረኢየሱስን ስብርብር አድርገው ደብድበው እኔ ያለሁበት ጭለማ ክፍል ወረወሯቸው ሲል ምስክርነቱን ሰጥቷል።
መነኮሳቱ የምንኩስና ልብሳችሁን አውልቁ በሚል ድብደባው እንደጸናባቸውም ተናግሯል።
መነኮሳቱ የእምነታቸው መገለጫ የሆነውን የምንኩስና ልብስ አውልቁ መባላቸው ደግሞ በርካታ የእምነቱ ተከታዮችን እያስቆጣ መሆኑ ተሰምቷል።
መነኮሳቱን እየደበደቡ ያሉት የዞን 5 ሃላፊ የሆኑት በርኽ የተባሉ አዛዥ መሆናቸው ታውቋል።
ይህ በእንዲህ እንዳለም የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ስልጣኑን አቷል ሲል የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 4ኛ ወንጀል ችሎት ብይን ሰቷል።
በፌደራል ደረጃን የተሰጠ ስልጣን የመሻሩ ጉዳይ በሕጉ የማን እንደሆነ ቢታወቅም አንድ ምድብ ችሎት ግን የክልሉን የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ስልጣኑን ነጥቆታል።
ለዚህ ያስቀመጠው ምክንያት ደግሞ አዲስ አበባና ድሬደዋ፣እንዲሁም ሶማሌ፣አፋር፣ደቡብና ቤንሻንጉል ክልሎች የክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤቶች የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤትን ስራ ደርበውና ወክለው እንዲሰሩ ስልጣን ስለተሰጣቸው ነው ይላል።
ከነዚህ ክልሎች ውጪ ያሉ የክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤቶች የከፍተኛ ፍርድ ቤት ስልጣንን አጥተዋል ሲል ብይን መስጠቱ ታውቋል።ፍርድ ቤቱ ይህንን ብይን ሲያሳልፍ ደግሞ ዛሬ የመጀመሪያው አይደለም በተደጋጋሚ ነው ሲሉ የኢሳት ምንጮች ይናገራሉ።
ችሎቱ ይህን ውሳኔ ያሳለፈው በእነ አስቻለው ደሴ መዝገብ የተከሰሱ 4 ግለሰቦች ወንጀል ፈጽማችኋል የተባልንው በአማራ ክልል በመሆኑ ጉዳያችንን ሊያየው የሚገባው የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ነው በሚል የክስ መቃወሚያቸውን በማቅረባቸው ነው።
በአብላጫ ድምጽ የተሰጠውን ይህንን ብይን የመሃል ዳኛው ዮሃንስ ጌስያብ ለሌሎች ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤቶች የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት በህግ መሰጠቱ የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይህን ስልጣን እንዲያጣ አያደርገውም ሲሉ የልዩነት ሃሳባቸውን አስፍረዋል።