(ኢሳት ዜና–ሕዳር 28/2010)
የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ኢየሩሳሌም የእስራኤል መዲና ነች ሲሉ እውቅና መስጠታቸውን ተከትሎ ሃማስ የአመጽ ጥሪ ማስተላላፉ ተሰማ።
የትራምፕን ውሳኔ ተከትሎም በኢየሩሳሌም፣በራማላህና በቤተልሄም ተቃውሞ ተቀስቅሷል።
የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ለኢየሩሳሌም እውቅና መስጠታቸውና በቴላቪቭ የሚገኘውን የአሜሪካ ኤምባሲ ወደ ኢየሩሳሌም ለማዛወር መወሰናቸው ከሀገራት መሪዎችና ከእስልምናው አለም ውግዘትን አስከትሏል።
እስራኤላውያንም ሆኑ ፍልስጤማውያን ኢየሩሳሌም በመዲናነት ትገባናለች ብለው ያምናሉ::ይህም ለዘመናት አጨቃጫቂ ጉዳይ ሆኖ ቆይቷል።
የሃማሱ መሪ እስማኤል ሃንየህ እንዳሉት የፕሬዝዳንት ትራምፕ ንግግር የሰላም ሂደቱን እስከመጨረሻው ቀብሮታል።
በአሜሪካ የሚደገፈው የእስራኤል ፖሊስም አዲስ አመጽ ይጠብቀዋል ብለዋል።
የሁለቱ ሀገራት ትብብርም ሰይጣናዊ ነው ሲሉ ገልጸውታል።
እንደ ሃማሱ መሪ ገለጻ የትራምፕ ንግግር በእስልምናም ሆነው በክርስትና ተከታዮች ዘንድ እንደ ተቀደሰች ስፍራ የምትቆጠረው ከተማ ላይ ጦርነት ማወጅ ነው።
በኢራን የሚደገፈው የፍልስጤም እስላማዊ የጅሃድ ቡድን መሪዎች ለአዲስ ትጥቅ ትግል መዘጋጀታቸውን አስታውቀዋል።
ናፌት አዛምና አህመድ አልባታሽ እንዳሉት የፍልስጤም ባለስልጣናት ከእስራኤል ጋር ያላቸውን ማንኛውንም ትብብር እንዲያቆሙ፣ለእስራኤል የሰጡትን እውቅና እንዲሰርዙ እንዲሁም በኦስሎ የተደረገውንና ለሰላም ድርድሩ መሰረት የሆነውን ስምምነት እንዲሽሩ ጠይቀዋል።
የትራምፕ ውሳኔ ለአስርት አመታት የቆየውን የአሜሪካ የውጪ ፖሊሲ የቀየረ ሲሆን ቀድሞውኑ ችግር ውስጥ ያለውን የሰላም ድርድር ጭራሹኑ እንዲቆም ያደርጋል የሚል ስጋትን ፈጥሯል።
ትራምፕ ግን ምንም አዲስ ነገር አይደለም በምርጫ ወቅት ቃል የገባሁትን ነው የፈጸምኩት ብለዋል።
ያለውን እውነታ የመቀበል ጉዳይ ነው፣መደረግ ያለበት ትክክለኛ ውሳኔ ነው ሲሉ ተደምጠዋል።
በቤተልሄም የተነሳውን ግጭት የእስራኤል ፖሊሶች የጎማ ጥይት፣አስለቃሽ ጋዝና ውሃ በመርጨት ለመበተን ሲሞክሩ ታይተዋል።
በራማላህ ተቃዋሚዎች በፖሊስ ላይ ድንጋይ ሲወረውሩና ጎማ ሲያቃጥሉ ውለዋል።
የእስራኤልና የአሜሪና ባንዲራንም አቃጥለዋል።
የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤኒያሚን ናታንያሁ የውጪ ዲፕሎማቶችን ሰብስበው ሌሎች ሀገራትም እውቅና ለመስጠት እንደተዘጋጁ ተናግረዋል።
የአሜሪካ ቁልፍ አጋር የሆኑት እንግሊዝና አውስትራሊያ የትራምፕን ውሳኔ እንደማይደግፉት ግልጽ አድርገዋል።
የእስልምና ሀገራት መሪዎች ግን ትራምፕን አውግዘዋል።
የቱርኩ ጠቅላይ ሚኒስትር ቢናሊ ይልድሪም የትራምፕ ውሳኔ የቦምብ ቀለበት እንደመሳብ ይቆጠራል ብለዋል።