(ኢሳት ዜና–ሕዳር 27/2010)
የአዲስ አበባ ከተማ መስተዳድር ነባርና ታሪካዊ አካባቢዎችን ማፍረስ ጀመረ።
ገዳም ሰፈርና ጌጃ ሰፈርን ጨምሮ አምስት ነባር ሰፈሮች ሙሉ ለሙሉ ይፈርሳሉ።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በ2010 ከያዘው ከ40 ቢሊየን ብር አመታዊ በጀት ውስጥ 30 ቢሊየን ብሩን ከማዘጋጃ ቤትና ግብር ነክ ገቢዎችን ከሕብረተሰቡ በቀጥታ የሚሰበስበው መሆኑ ይታወቃል።
ከዚህ ገቢ ውስጥ ከፍተኛ ድርሻውን የያዘው ነባር መሬቶችን በማስለቀቅ መሬቱን በመሸጥ የሚያገኘው እንደሆነ መረጃዎች ያመላክታሉ።
የቀድሞ የአዲስ አበባ አስተዳደር ከተማ ልማት ቢሮ አማካሪ ዶክተር ግዛቸው ቴሶ ለኢሳት እንደገለጹት አገዛዙ ነባርና ታሪካዊ አካባቢዎችን የሚያፈርሰው በዋናነት የነዋሪውን ማህበራዊ ትስስር ለመበጣጠስ በማሰብ ነው ብለዋል።
የህብረተሰቡ ዲሞግራፊ በተቀየረ ቁጥር አዲስ አበባ የስርአቱ ተቃውሞ ማዕከል መሆኗ ሊቀንስ እንደሚችል አጋዛዙ እምነት እንዳለው ተናግረዋል።
የአዲስ አበባ ከተማ መስተዳድር በከተማዋ ነዋሪ ተቃውሞና ቅሬታ ለሁለት አመት አቋርጦት የነበረውን ነባርና ታሪካዊ የመዲናይቱን አካባቢዎች ማፍረስ መጀመሩን ለኢሳት የደረሰው መረጃ አመልክቷል።
በአራዳ ክፍለ ከተማ “እሪ በከንቱ” በሚባለው አካባቢ ለነዋሪዎች ምንም አይነት ማስጠንቀቂያ ሳይሰጣቸው ቤታቸው በመፍረሱ ምክንያት ሕጻናት ልጆቻቸውን ይዘው በላስቲክ መጠለያ ቤት ለመኖር መገደዳቸውን ለማየት ተችሏል።
በ2004 ይፈርሳሉ ተብለው የነበሩ አካባቢዎችን እስከ ታህሳስ መጨረሻ ሙሉ በሙሉ እንደሚያፈርስ የከተማው መሬት ልማት ማኔጅመንት መግለጹን ተከትሎ በሚቀጥሉት ወራት ከስድስት በላይ ነባር ቦታዎች እንዲፈርሱ ትዕዛዝ መተላለፉንም ለማወቅ ተችሏል።
የኢሳት የአስተዳደሩ የውስጥ ምንጮች እንደገለጹት በልደታ፣ቂርቆስ፣የካ፣አራዳና አዲስ ከተማ ክፍለ ከተሞች የሚገኙት “እሪ በከንቱ”፣ “ገዳም ሰፈር”፣ “ጌጃ ሰፈር”፣ “ሾላና መገናኛና”፣ “ካዛንችስ ቶታል” በአስቸኳይ እንዲፈርሱ ለክፍለ ከተሞችና ወረዳ መስተዳድሮች መመሪያ መተላለፉ ታውቋል።