(ኢሳት ዜና–ሕዳር 19/2010) የመከላከያ ሰራዊት አባላት በወገን ቀርቶ በጠላት ላይ የማይደረግ ኢ ሰብአዊ ድርጊት ፈጽመዋል ሲል የቦረና አስተዳደር ቅሬታውን አቀረበ።
ድርጊቱን የፈጸሙ የመከላከያ አባላት ተላልፈው እንዲሰጡና ለህግ እንዲቀርቡም ጠይቋል።
በኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት የቦረና ዞን አስተዳደር ጽሕፈት ቤት በሕዳር 14/2010 ለጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት፣ለመከላከያ ሚኒስቴርና ለኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት በጻፈው ደብዳቤ የመከላከያ ሰራዊት ያደረሰውን ኢ-ሰብአዊ ድርጊት በዝርዝር አስፍሯል።
ደብዳቤው በቦረና ዞን ድሬ ወረዳ ሶዶ ቀበሌ ግበሬ ማህበር ህብረተሰብ ላይ የደረሰውን ኢ-ሰብአዊ ድርጊት ይመለክታል የሚል ርዕስን ይዟል።
የመከላከያ ሰራዊቱ አባላት ጥቅምት 2/2010 የገበሬ ማህበሩ ነዋሪዎች የሆኑ 3 ሰዎችን ኢ-ሰብአዊና አሰቃቂ በሆነ መልኩ በጥይት ደብድበው ሲገድሉ 19 ያህል ነዋሪዎችን ደግሞ በከባድ ሁኔታ ማቁሰላቸውን በደብዳቤው ላይ የሰፈረው ጽሁፍ ያመለክታል።
ከባድ የመቁሰል አደጋ ከደረሰባቸው ውስጥ ከ70 አመት በላይ የሚሆኑ አዛውንቶች፣ ሴቶችና ዕድሜያቸው ከ10 አመት በታች የሆኑ ህጻናት እንደሚገኙበትም ታውቋል።
ለኢ-ሰብአዊና አሰቃቂ ድርጊቱ መንስኤ የሆነው ከዚህ በፊት በቀበሌ ገበሬ ማህበሩ የጭነት ተሽከርካሪዎች አልፈው ስለማያውቁና ባለተለመደ ሁኔታ የተገኘው ተሽከርካሪ የኮንትሮባንድ እቃ ጭኖ ሊሆን ይችላል በሚል ህብረተሰቡ ተፈትሾ እንዲያልፍ በመጠየቁ መሆኑን የዞኑ አስተዳደር የላከው ደብዳቤ አመልክቷል።
የመከላከያ አባላቱ የሕዝቡን ጥያቄ ተቀብለው ሁኔታውን ማስረዳት ሲኖርባቸው “ኑ አብረን እንፈትሽ” በማለት ህዝቡን አታለው እንዲጠጋ ካደረጉት በኋላ ርምጃውን መውሰዳቸውን ደብዳቤው ይገልጻል።
የመከላከያ ሰራዊቱ በገበሬ ማህበሩ ህዝብ ላይ ጭካኔ የተሞላበት ርምጃ ካደረሰ በኋላ ህዝቡን ከማረጋጋት ይልቅ ይባስ ብሎ የማስፈራራት ርምጃ ወስዷል በማለት በዞኑ አስተዳዳሪ አቶ ሊበን አራሮ የወጣው ደብዳቤ ያመልክታል።
ከድርጊቱ በኋላ የሰራዊቱ አባላት ዲሽቃ፣ዙ-23፣መትረየስና ስናይፐር ጭነው በመምጣት ህብረተሰቡን በማወክና በማስጨነቅ በወገን ቀርቶ በጠላት ላይም የማይደረግ ኢ-ሰብአዊ ድርጊት አድርሰዋል ይላሉ የዞኑ አስተዳዳሪ በጻፉት ደብዳቤ።
በመሆኑም ይህንን አሰቃቂ ድርጊት በንጹሃን ህብረተሰባችን ላይ ያደረሱ የመከላከያ አባላት ተላልፈው እንዲሰጡንና ለሕግ እንዲቀርቡ እንጠይቃለን ሲሉ አቶ ሊበን አራሮ በጻፉት ደብዳቤ ላይ አስፍረዋል።