(ኢሳት ዜና–ሕዳር 11/2010)ሜቴክ በአቶ አርከበ እቁባይ ትዕዛዝ ከኦሮሚያ ክልል በህገወጥ መንገድ የድንጋይ ከሰል በማውጣት እየሸጠ እንደሆነ በፓርላማ ተገለጸ።
ጥሬ ሐብቱ እየተበዘበዘበት ያለው ህዝብም ተቃውሞውን በማሰማት ላይ ነው።
በሕወሃቱ ጄኔራል ክንፈ ዳኘው የሚመራው የኢትዮጵያ ብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን /ሜቴክ/በሕግ ከተቋቋመበትና ከተሰጠው ስልጣን ውጪ ከኦሮሚያ የድንጋይ ከሰል በማውጣት እየሸጠ መሆኑ የፓርላማ ቋሚ ኮሚቴ አባላት እንዳሳሰባቸው ተናግረዋል።
የመንግስት ልማት ድርጅቶች ቋሚ ኮሚቴ አባላት የሜቴክን የ2010 በጀት አመት እቅድና አንደኛ ሩብ አመት አፈጻጸም ሲገመግሙ ኮርፖሬሽኑ በኦሮሚያ ክልል ኢሉባቦር ዞን ያዩ ወረዳ የድንጋይ ከሰል ከስልጣኑ ውጪ በማውጣት እየሸጠ መሆኑ ሕብረተሰቡን ቅሬታ ውስጥ እንደከተተው ተናግረዋል።
የቋሚ ኮሚቴው አባላት ሜቴክ ከተቋቋመበት አላማ ውጪ የድንጋይ ከሰል እያመረተ በመሸጥ ላይ መሆኑ ከአካባቢው ህብረተብ ጋር ቅራኔ ውስጥ እያስገባው ነው።
ይህንን ስራ ሜቴክ እንዲሰራ የተቋቋመበት ህግ የፈቅድለታል ወይ በማለትም አባላቱ ጠይቀዋል።
ቋሚ ኮሚቴው ላቀረበላቸው ጥያቄ ምላሽ የሰጡት የሜቴክ ምክትል ዋና ዳይሬክተር ብርጋዴር ጄኔራል ጥጋቡ ፈትለ ሜቴክ የድንጋይ ከሰሉን እንዲሸጥ የመከሩን የጠቅላይ ሚኒስትሩ አማካሪ ዶክተር አርከበ እቁባይ ናቸው ብለዋል።
የህጋዊነትና ከአካባቢው ህብረተሰብ ጋር ሜቴክ ቅራኔ ውስጥ ገብቷል የሚለውን ከመመለስ የተቆጠቡት ብርጋዴር ጄኔራሉ ይቁም ከተባለ ሊቆም ይችላል በማለት ምላሽ ሰጥተዋል።
ከአቶ አርከበ እቁባይ ጋር በቅርበት የሰሩ ባለሙያዎች እንደገለጹት አቶ አርከበ እንደዚህ አይነት ትዕዛዝ ሲሰጡ የመጀመሪያቸው አይደለም።
ከዚህ በፊት ጂ ቲ ዜድ የሚባለው ድርጅት አፈር ከኦሮሚያ እየጫነ ወደ ትግራይ እንዲወስድ አድርገዋል።
የአካባቢውን ጥሬ ሀብት እየበዘበዙ ወደ ሌላ ቦታ መውሰድና መሸጥ ቅኝ ገዥዎች ሲከተሉት የነበረ አሰራር መሆኑን ሙያተኞቹ ገልጸዋል።
ራስን በራስ ማስተዳደር ከሚባለውም ጋር እንደሚጋጭ አክለው ተናግረዋል።
ባሳለፍንው ሳምንት መጨረሻ ላይ ጎንደር በተካሄደ የሕወሃት ብአዴን ጉባኤ ላይ አቶ በረከት ስምኦን የትኛውም የኢትዮጵያ ብሔር ሌላ ያስተዳድረኛል ሊል አይችልም።
ሁሉም ራሱን በራሱ የሚያስተዳድር ነው በማለት መግለጻቸው የሚታወስ ነው።
አቶ አርከበ እቁባይ በይፋ የሚታወቅ የዕዝ ሰንሰለት የሚከተል ስልጣን እንደሌላቸው ይታወቃል።
የጠቅላይ ሚኒስትሩ አማካሪ በመሆን እንደሚሰሩም ሲገለጽ ቆይቷል።