በአሜሪካ ቴክሳስ በአንድ ቤተክርስቲያን ላይ በተፈጸመ ጥቃት 26 ሰዎች ሞቱ

(ኢሳት ዜና–ጥቅምት 27/2010) በአሜሪካ ቴክሳስ ግዛት በአንድ ቤተክርስቲያን ላይ በተፈጸመ ጥቃት 26 ሰዎች ሲሞቱ 20 ደግሞ ቆሰሉ።

የሟቾቹ እድሜ ከ18 ወር ሕጻን እስከ 77 ባለው ክልል ውስጥ ነው በተባለው በዚህ ጥቃት 8 የአንድ ቤተሰብ አባላትም መገደላቸው ታውቋል።

ጥቃቱን የፈጸመውም የ26 አመት እድሜ ያለውና የአእምሮ ታማሚ ሳይሆን አይቀርም የተባለው ዴቪን ኬሊ የተባለ የቀድሞ አየር ሃይል ባልደረባ መሆኑ ታውቋል።

በአሜሪካ ቴክሳስ ሳውዘርላንድ ስፕሪንግ በተባለ ከተማ በሚገኘው የባፕቲስት ቤተክርስቲያን በተፈጸመው ጥቃት የሞቱት 26 ሰዎች እድሜም ከ18 ወር ሕጻን እስከ 77 ባለው ክልል ውስጥ የሚገኝ መሆኑን መረጃዎች አመልክተዋል።

በቤተክርስቲያኗ ላይ ተፈጸመ የተባለውን ጥቃት ያደረሰው የ26 አመት እድሜ ያለውና የአእምሮ ታማሚ ሳይሆን አይቀርም ተብሎ የሚጠረጠረው ዴቪን ኬሊ የተባለ ግለሰብ እንደሆነም ለማወቅ ተችሏል።

በጥቃቱ ወቅት አንዳንድ ወላጆች በሰውነታቸው በመሸፈን ልጆቻቸውን ለማዳን የሞከሩ ሲሆን ጥቃት ፈጻሚው በቤተክርስቲያኒቱ የኋላ በር በመግባት እየተኮሰ በፊት በር ወጥቶ መኪናውን አስነስቶ ሲያመልጥ ሁለት ሰዎች በፍጥነት ሲከታተሉት መኪናው ተጋጭቶ ቆሟል።

በኋላም በጥይት መመታቱ የታወቀ ሲሆን በራሱ ላይ ይተኩስ ወይም በሌሎች ሰዎች በተተኮሰ ጥይት ይሙት ለማወቅ ምርመራ በመደረግ ላይ ነው።

በመኪናው ውስጥም በርካታ መሳሪያዎች ተገኝተዋል።

በቤተክርስቲያኒቱ የገዳዩ የሚስት ዘመዶች እንደሚያዘወትሩም ለማወቅም ተችሏል።እንደ ሲ ኤን ኤን ዘገባ ከሆነም ገዳይ በባለቤቱ እናት ብዙ ጊዜ ይበሳጭ እንደነበርም ለማወቅ ተችሏል።

ከሟቾቹ መካከል የ14 አመት ታዳጊ የሆነችው የፓስተሩ ልጅ ስትገኝ ሌሎች 8 የአንድ ቤተሰብ አባላትም በጥቃቱ ህይወታቸው ማለፉ ታውቋል።

ግለሰቡ ከዚህ በፊት በባለቤቱና በልጆቹ ላይ በፈጸመው ጥቃትና እንዲሁም በአየር ሃይል ውስጥ አባል በነበረበት ጊዜ በፈጸመው የስነስርአት ማጉደል ተከሶ ጥፋተኛ በመባሉ መሳሪያ ገዝቶ ለመታጠቅ ሕጉ እንደማይፈቅድለት የሚያሳዩ መረጃዎች በመውጣት ላይ ናቸው።

በአሜሪካ አጨቃጫቂ ከሆኑት ጉዳዮች አንዱ የሆነው የሰዎች መሳሪያ የመያዝ መብት ይከበር ወይንስ ቁጥጥር ይደረግበት የሚለው ሙግት እንደገና አገርሽቶበታል።

በሀገሪቱ በሚፈጠሩ እንዲህ አይነትና ሌሎችም ጉዳዮች ላይ ከመቀጽበት የግል አስተያየታቸውን በመስጠት የሚታወቁት የሀገሪቱ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ገዳዩ ድርጊቱን የፈጸመው ከአእምሮ ጋር በተያያዘ ችግር እንጂ መሳሪያ የመያዝ መብት መኖር ጉዳይ አይደለም ሲሉ ተናግረዋል።

መሳሪያ የመያዝ መብት አቀንቃኞችና ከ5 ሚሊየን በላይ አባል ያሉት የብሔራዊ ጠመንጃ ማህበር አባላት ዘንድ ተቀባይነትና ድጋፍ ያላቸው ፕሬዝዳንት ትራምፕ ግለሰቡ የአእምሮ ህመመተኛ ስለሆነ የፈጸመው እንጂ መሳሪያ በመያዙ የደረሰ አደጋ አይደለም ሲሉ ተደምጠዋል።

በኢሲያ ጉብኝት በማድረግ ላይ ኣያሉ ጃፓን ላይ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ሌሎች መሳሪያ በመያዛቸው ግለሰቡ የበለጠ ጉዳት ከማድረሱ በፊት ሊያስቆሙት ችለዋል ብለዋል።

መሳሪያ የመታጠቅ መብት መከበር መከራከሪያቸውን ለማቅረብ ሞክረዋል ብሏል ኤቢሲ በዘገባው።

በቴክሳስ የደረሰው ጥቃት በአሜሪካ በቤተክርስቲያናት ላይ ከደረሱ ሶስት አስከፊ ጥቃቶች አንዱ ሆኖ ተመዝግቧል።

በሰኔ 2015 በሳውዝ ካሮላይና አንድ የነጭ አክራሪ ወጣት የአፍሪካ አሜሪካውያን ቤተክርስቲያን ውስጥ ገብቶ ተኩስ በመክፈቱ ዘጠኝ ምዕመናንን ገድሏል።

ዲላን ሩፍ ለፈጸመውም ወንጀል በተያዘው የፈረንጆቹ አመት መግቢያ ላይ የሞት ፍርድ ተፈርዶበታል።