በኒዮርክ በደረሰው የሽብር ጥቃት 8 ሰዎች ሞቱ

(ኢሳት ዜና–ጥቅምት 22/2010) በኒዮርክ ትላንት አንድ ግለሰብ የእቃ መጫኛ መኪናን በመጠቀም ባደረሰው ጥቃት ስምንት ሰዎች ሲሞቱ ከ10 በላይ ቆሰሉ።

የሽብር ጥቃት ነው በተባለው በዚህ አደጋ ህይወታቸውን ካጡት መካከል ለጉብኝት የመጡ አምስት አርጀንቲናውያን ጓደኛሞች እንደሚገኙበት ታውቋል።

ጥቃቱን የፈጸመው የ29 አመቱ ኡዝቤክስታናዊ ከፖሊስ በተተኮሰ ጥይት ቆስሎ ወደ ሆስፒታል ተወስዷል።

የትላንቱን የኒዮርክ ጥቃት የ29 አመቱ የኡዝቤክስታን ተወላጅ የተከራየውን የእቃ መጫኛ መኪና ሰዎች በቢስኪሌት በሚጓዙበት መንገድ ላይ በፍጥነት አብርሮ ሲነዳ በወቅቱ በቢስኪሌትና በእግር ሲጓዙ የነበሩ ሰዎችን ደፍጥጦ ከገደለና ካቆሰለ በኋላ ከተማሪዎች መጓጓዣ አውቶቡስ አጋጭቶ ማቆሙ ተሰምቷል።

በዚህም የ8 ሰዎች ህይወት ሲያልፍ 10 ሰዎች ደግሞ ቆስለዋል።

የኒውጀርሲ ነዋሪ የሆነው የኡዝቤኪስታን ተወላጁ ሳይፋሎ ሳይፓቭ ጥቃቱን ከፈጸመ በኋላ አላህ አክበር እያለ ከመኪናው በመውረድ በያዘው ሁለት የውሸት ሽጉጦች በአካባቢው ያሉትን ሰዎችና ፖሊሶችን ሲያስፈራራ ቢቆይም የበስተኋላ ግን ከአንድ የኒዩርክ ፖሊስ በተተኮሰ ጥይት ተመቶ ወድቋል።

ግለሰቡ ሆዱ ላይ በጥይት ተመቶ በመቁሰሉም ወደ ሆስፒታል ተወስዷል።

እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ2010 ወደ አሜሪካ የመጣው ሳይፋሎ ሳይፓቭ ጥቃቱን የፈጸመው በአይ ሲ ስ ስም መሆኑን መኪናው አቅራቢያ በተወው የማስታወሻ ወረቀት ለማወቅ ተችሏል።

የኒዮርክ ከተማ ከንቲባ ቢል ዲብላሲዮ ድርጊቱን በሰላማዊ ሰዎች ላይ ያነጣጠረ የሽብር ጥቃት ሲሉ ኮንነውታል።

የጸጥታ ባለስልጣናት በሽብር ጥቃትነት የተመዘገበውን ይህን ድርጊት በመመርመር ላይ መሆናቸውን አስታውቀዋል።

የእቃ መጫኛ መኪና ለሽብር ጥቃት ሲውል ከለንደንና ከፈረንሳይ በኋላ የኒዮርኩ ለሶስተኛ ጊዜ ሲሆን ጥቃቱ ከ16 አመት በፊት በመንታ ሕንጻዎች ላይ በሁለት አውሮፕላኖች ከደረሰው ጥቃት በኋላ አስከፊው ነው ተብሏል።

የትናንትናውም ጥቃት ከ16 አመት በፊት ለደረሰው ጥቃት በተሰራውና “ፍሪደም ታወር” በመባል በሚታወቀው መታሰቢያ አቅራቢያ እንደተፈጸመ ለማወቅ ተችሏል።

ከሟቾቹ ውስጥም አምስቱ ለጉብኝት የመጡ አርጀንቲናውያን ጓደኛሞች ሲሆኑ ወደ ኒዮርክ የመጡትም ከኮሌጅ የተመረቁበትን 30ኛ አመት ለማክበር እንደነበር የሀገሪቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታውቋል።

የኒዮርክ ነዋሪዎች ጥቃቱ ቢፈጸምም ትላንት የተከበረውን የሀለዊን በአል አክብረዋል።

ከበአሉ ተሳታፊዎች አንዳንዶቹ ለሲ ኤን ኤን በሰጡት አስተያየት ሽብርተኞች ባህላችንን አኗኗራችንንና የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴያችንን ሊያቆሙ አይችሉም ብለዋል።

በበአሉ ላይ የተገኙት የከተማዋ ከንቲባም አሜሪካኖች በአሸባሪዎች ጥቃት ምክንያት ማንነታችንንና ባህላችንን የምንቀይር ከሆነ ሽብርተኞች አሸነፉ ማለት ነው ብለዋል።