የኦህዴድ ድርጅታዊ ጉባኤ በላይኛውና በታችኛው ካድሬ አጀንዳ አለመስማማት ተራዘመ

(ኢሳት ዜና–ጥቅምት 22/2010)በአዳማ እየተካሄደ ያለው የኦህዴድ ድርጅታዊ ጉባኤ በላይኛውና በታችኛው ካድሬ አጀንዳ አለመስማማት ተራዘመ።

በጉባኤው የግል ስልክን ጨምሮ ማንኛውም የኤሌክትሮኒክስ መሳሪያ እንዳይገባ ጥብቅ ፍተሻ ተደርጓል።

እሁድ ጥቅምት 19/2010 በአዳማ ከተማ ገልማ አባገዳ አዳራሽ በአንድ ቀን ይጠናቀቃል ተብሎ የተጀመረው የኦህዴድ ድርጅታዊ ጉባኤ በድርጅቱ ከፍተኛ አመራርና የጉባኤው ተሳታፊዎች መካከል መግባባት ባለመቻሉ እስከ ጥቅምት 23 ድረስ ሊራዘም መቻሉን የኢሳት የውስጥ ምንጮች አስታውቀዋል።

የጉባኤው ተሳታፊዎች የክልሉንም ሆነ የሀገሪቱን ዘርፈ ብዙ ችግሮች ኪራይ ሰብሳቢዎች፣ጠባቦች፣መልካም አስተዳደር፣አገልግሎት አሰጣጥ በማለት መሸፋፈን የማይቻልበት ደረጃ መደረሱን ገልጸዋል።

ሀገሪቱን ለመበታተን የተቃረቡ ችግሮችን በግልጽነት ፍርጥርጥ አድርጎ ለመነጋገር የበላይ አመራሮች ዝግጁነት ይጎድላቸዋል ያሉት ተሳታፊዎች ለውውይት የቀረበው አጀንዳ አይመጥንም ብለዋል።

በተለይም የክልሉን ወቅታዊ የጸጥታ ችግር፣ኦህዴድ ከኢህአዴግ አባል ድርጅቶችና ሌሎች ፓርቲዎች ጋር ያለው ግንኙነት፣በፌደራል ስርአቱ በኦሮሞ ህዝብ ላይ እየደረሰ ያለው በደል ሳይሸፋፈን ውይይት ሊደረግበትና ውሳኔ ሊሰጥበት ይገባል ብለዋል።

የጉባኤው ቃል አቀባይና የኦሮሞ ኮሚኒኬሽን ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ አዲሱ አረጋ በበኩላቸው የጥልቅ ተሃድሶ ከተጀመረ በኋላ በኦሮሞ ህዝብ ውስጥ እየታየ ያለው የአንድነት፣የመተባበርና በአንድነት የመቆም መንፈስ እየተጠናከረ መጥቷል ብለዋል።

አቶ አባዱላ ገመዳ በበላይነት ይመሩታል ተብሎ የሚጠበቀው የኦሮሞ የኢኮኖሚ አብዮት ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።

ከድርጅት አኳያ የኦህዴድን ፖለቲካዊ ቁመና ለማስተካከል የሚያስችሉ የድርጅታዊ መዋቅር፣ አሰራርና አደረጃጀት ለውጥ የሚደረግ መሆኑን ገልጸዋል።

ምን አይነት ድርጅታዊ መዋቅርና አደረጃጀት እንደሚኖር ግን በዝርዝር ከመግለጽ ተቆጥበዋል።

የኢሳት የውስጥ ምንጮች እንደገለጹት በጉባኤው የእረፍትና የምሳ ሰአቶች የጉባኤው ተሳታፊዎች አቶ አባዱላ ገመዳን በመክበብ በውሳኔያቸው መኩራታቸውን ሲገልጹ ተስተውለዋል።

ሲያመሰግኗቸውና ከጎናቸው እንደሚቆሙ ቃል ሲገቡ እንደነበርም ምንጮቹ ጨምረው ገልጸዋል።

አቶ አባዱላ ገመዳ የሕዝቤና የድርጅቴ ክብር እየተነካ በስልጣን መቆየት አልፈልግም በማለት ከአፈጉባኤነት ለመልቀቅ ጥያቄ ማቅረባቸው የሚታወስ ነው።

በውስጥም በውጭም ያለው የኦሮሞ ህዝብ በአንድነት የመቆም መንፈስ እየተጠናከረ መጥቷል ማለታቸውም ይታወሳል።