(ኢሳት ዜና–ጥቅምት 21/2010)ከስፔን በመገንጠል ነጻነቷን ያወጀችው ካታላን መሪ ከ5 ሚኒስትሮቻቸው ጋር ከሀገር ተሰደዱ።
ስፔን ግዛቲቱን በመቆጣጠር የሀገሪቱን ባላስልጣናት በአዲስ መሪዎች የተካች ሲሆን የካታላን የራስ ገዝ መብትም ለጊዜው ታግዷል።
ሙሉ በሙሉ የስፔን ግዛት ሆና እንድትቀጥል የሚያስችሉ ርምጃዎችም ተጠናክረው ቀጥለዋል።
ባለፈው አርብ የካታላን ነጻነትን በይፋ መታወጅ ተከትሎ ቤልጂየም ብራስልስ የደረሱት የካታላን መሪ ካርለስ ፑጂሞንት ነጻነት ያወጁበትን ሀገር ጥለው ከሀገር ስለመውጣታቸው ከጋዜጠኞች ለቀረበላቸው ጥያቄ ወደ ሀገሬ እመለሳለሁ ሲሉ አጭር ምላሽ ሰጥተዋል።
ወደ ሀገራቸው መቼ እንደሚመለሱ ግን ያሉት ነገር የለም።
ለመመለስም ከስፔን መንግስት ዋስትና እንደሚፈልጉ ተናግረዋል።
ነጻነትን አውጀው በቀናት ሀገር ጥለው ከወጡት የካታላን መሪ ካርለስ ፑጂሞንት በተጨማሪ አምስት ሚኒስትሮች በተመሳሳይ ተሰደው ብራስልስ ደርሰዋል።
የስፔን መንግስት ነጻነቱን አግዶ የነበረውንም የራስ ገዝ መብት ሽሮ ባለስልጣናቱን በማባረር በወሰደው ርምጃ ሀገሪቱን ጥለው መሪያቸውን ተከትለው ከተሰደዱት 5 ሚኒስትሮች የሀገር ውስጥ ጉዳይና የጤና ሚኒስትሩ ይገኙበታል።
የካታላን መሪዎች ነጻነትን በማወጅ በወሰዱት ርምጃ የአካባቢ ገዥዎችን ጨምሮ 150 ባለስልጣናት የተባረሩ ሲሆን ክስ እንደሚመሰረትባቸውም እየተጠበቀ ይገኛል።
የስፔን የጸጥታ ሃይሎች ካታላን በመግባት ይዞታቸውን እየተቆጣጠሩ ሲሆን የካታላን ፖሊስ ጣቢያዎችን እየወረሩ በፖሊስ ተሽከርካሪዎች ላይ ጥቃት እየፈጸሙ ነው የሚል ክስም እየቀረበባቸው ነው።
የስፔን መንግስት የነጻነት ጥያቄውን ውድቅ በማድረግ እንዲሁም የነበረውንም የራስ ገዝ መብት በማገድ እየወሰደ ያለውን ርምጃ በመፍራት ከሀገር ጥለው የተሰደዱት የካታላኑ መሪ ካርለስ ፑጂሞንት ሊያስሩኝ ነው ሲሉም ስጋታቸውን ገልጸዋል።
የስፔን መንግስት እስከ 30 አመት የሚደርስ እስራት የሚያስፈርድ ክስ እያቀነባበረብኝ ነው ያሉት ካርለስ ፑጂሞንት በዚሁ አጋጣሚ ጥገኝነት የመጠየቅ ፍላጎት እንዳላቸውም ምልክት ሰጥተዋል።
ሁሉንም አማራጮች አያለሁ ሲሉ መናገራቸውም ተመልክቷል።
130ኛው የካታላን ፕሬዝዳንት በመሆን ከሁለት አመት ያነሰ ጊዜ በስልጣን ላይ የቆዩት ካርለስ ፑጂሞንት ጥገኝነት እንዳያገኙና ተላልፈው እንዲሰጡ የስፔን መንግስት ፍላጎት እንደሆነም ከዘገባዎች መረዳት ተችሏል።