(ኢሳት ዜና–ጥቅምት 21/2010) በሰሜን ጎንደር ህዝበ ውሳኔ አንፈልግም ባሉት አራት ቀበሌዎች ላይ መንግስት ውሳኔ አስተላለፈ።
በአንድነት መኖርን እንመርጣለን ባሉት በእነዚህ አራት ቀበሌዎች ላይ በተላለፈው ውሳኔ መሰረት ሁለቱ በቀደመው አስተዳደር ሁለቱ ደግሞ በቅማንት አዲስ መዋቅር ስር እንዲሆኑ ተደርገዋል።
ከህዝብ ፍላጎት ውጪ በህወሀት መንግስት ውሳኔ የተሸነሸኑት ቀበሌዎች ጉዳይ በአካባቢው አዲስ ውጥረት እንዲቀሰቀስ ሊያደርግ እንደሚችል እየተነገረ ነው።
ህወሀት ውዝግብ የተፈጠረባቸው አካባቢዎች ይላቸዋል። ህዝቡ ግን ውዝግብ የለም አንድ ነን የሚለውን አቋሙን ከመግለጽ ወደ ኋላ ብሎ አያውቅም።
ይህንንም በቅርቡ ባሳየው ህዝበ ውሳኔ ላይ አረጋግጧል። ሆኖም የህወሀት መንግስት ሁለቱን ማህበረሰቦች ለመለያየት የያዘውን አጀንዳ ከዳር ለማድረስ እንቅስቃሴውን አላቋረጠም።
ህዝበ ውሳኔ አያስፈልገንም ብለው አቋም ላይ ደርሰው በነበሩ አራት ቀበሌዎች ላይ ውሳኔ መሰጠቱን ሪፖርተር ጋዜጣ ዘግቧል።
በእነዚህ ቀበሌዎች የሚኖሩት ሁለቱ ማህበረሰቦች ምርጫ ቦርድ በአካባቢያቸው ህዝበ ውሳኔውን እንዳያደርግ በማሳሰባቸው ሳይካሄድ መቅረቱ የሚታወስ ነው።
የኢሳት ምንጮች እንደገለጹት በመስከረም 7 የተካሄደው የ8ቱ ቀቤሌዎች ህዝበ ውሳኔ የህወሀትን መንግስት አስደንግጦታል።
ከ8ቱ ቀበሌዎች አንደኛው አዲስ በተካለለው የቅማንት አስተዳደር ስር እንዲሆን መወሰኑ የህዝብ ፍላጎት አይደለም በሚል የተቃወሙ ነዋሪዎች አቤታቱ አቅርበው ውጤት በመጠባበቅ ላይ ባሉበት ወቅት ነው የህወሀት መንግስት ህዝበ ውሳኔ አያስፈልገንም ባሉት አራት ቀበሌዎች ላይ ውሳኔ ማስተላለፉ የተሰማው።
በዚህም መሰረት ከአራቱ ቀበሌዎች ሁለቱ በቀደመው፡ ሁለቱ ደግሞ አዲስ በሚካለለውና የህወሀት መንግስት በሚደግፈው የቅማንት አስተዳደር ስር እንዲሆኑ ተወስኗል።
በመስከረም ሰባቱ ህዝበ ውሳኔ ያልተሳተፉት አራቱ ቀበሌዎች በወቅቱ ምርጫ ቦርድ ወደ አካባቢያችን እንዳይመጣ በሚል ማስጠንቀቃቸው የሚታወስ ነው።
ቀደም ሲልም ያለህዝበውሳኔ በህወሀት መንግስት ፍላጎት ብቻ 42 ቀበሌዎች ወደ ቅማንት አስተዳደር ስር እንዲገቡ መደረጉ ቁጣን ቀስቅሷል።
ታዛቢዎች እንደሚገልጹት የህወሀት መንግስት በሁለቱ ማህበርሰቦች መሃል ጥላቻን በመፍጠር በአካባቢው የሚፈልጋቸውን መሬቶች ለመቆጣጠር አቅዶ የተንቀሳቀሰ ነው።
በቅማንት ማህበርሰብ ላይ ተንጠልጥሎ የራስን ድብቅ ዓላማ ለማስፈጸም የሚደረገውን የህወሀት ሴራ ሁለቱም ህዝቦች እንዲያከሽፉት ጥሪ እየተደረገ ነው።
ያለህዝበ ውሳኔ በህወሀት ፍላጎት ለሁለት አስተዳደሮች ተከፋፍለው የተሰጡት አራቱ ቀበሌች ከወዲሁ በውጥረት ውስጥ የገቡ ሲሆን ተቃውሞ ይቀሰቀሳል የሚል ስጋትም ተፈጥሯል።