(ኢሳት ዜና–ጥቅምት 21/2010) የትግራይ ክልላዊ መንግስት በኦሮሚያ ብሮድካስቲንግ ኔትወርክ ላይ ያቀረበውን ቅሬታ ተከትሎ የክልሉ ሚዲያ ቦርድ ርምጃ መውሰዱ ተገለጸ።
ቦርዱ የትግራይ አስተዳደር ያቀረበውን ቅሬታ ተከትሎ ዘገባውን በሰራው ጋዜጠኛ ላይ ርምጃ መውሰዱን የገለጸ ሲሆን ስለተወሰደው ርምጃ ግን ያለው ነገር የለም።
የትግራይ ክልል መንግስት በጥቅምት 20/2010 በጻፈው ደብዳቤ የኦሮሞ ብሮድካስቲንግ ኔትወርክ/ኦቢኤን/በሚያቀርባቸው ዘገባዎች ላይ በተደጋጋሚ ቅሬታዎችን ቢያቀርብም ተቋሙም ሆነ የሚመለከታቸው አካላት አዎንታዊ ምላሽ እንዳልሰጡት ገልጿል።
የትግራይ ክልል ኮሚኒኬሽን ጽህፈት ቤት አደገኛና “በአስቸኳይ መታረም ያለበት ዘር ተኮር ዘገባ” በሚል ርዕስ ያወጣው ይህ ደብዳቤ የሚመለከታቸው አካላት አስቸኳይ ምላሽ እንዲሰጡበትም ይጠይቃል።
ይህ የማይሆን ከሆነ ግን እኛም በራሳችን ሚዲያዎች ወደ ማውገዝ እንሸጋገራለን ሲሉ የትግራይ ኮሚኒኬሽኝ ቢሮ ሃላፊ አቶ ገብረሚካኤል መለስ ማስጠንቀቃቸው ይታወሳል።
ይህን ተከትሎም የኦሮሚያ መስተዳድር ኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ሃላፊ አቶ አዲሱ አረጋ ለቢቢሲ አማርኛው ክፍል መግለጫ ሰጥተዋል።
ሃላፊው በመግለጫቸው የክልሉ ሚዲያ ቦርድ ጥቅምት 20/2010 የትግራይ አስተዳደር ያቀረበውን ቅሬታ ተከትሎ ባካሄደው ግምገማም ዘገባውን በሰራው ጋዜጠኛ ላይ ርምጃ ተወስዶበታል ብለዋል።
አስተዳደራዊ ርምጃው ምን እንደሆነ ግን ከመናገር ተቆጥበዋል።
አቶ አዲሱ አረጋ በትግራይ ሕዝብና በኦሮሞ ሕዝብ መካከል ልዩነት መፍጠር አይቻልም ሲሉም አክለዋል በመግለጫቸው።
በጥርጣሬ የተያዙ ግለሰቦችን ከትግራይ ህዝብ ጋር አገናኝቶ መዘገብ የተሳሳተ ነው በማለት ራሳቸው የሚያስተዳድሩትና የቦርድ አመራር የሆኑበት ሚዲያ ከፍተኛ ስህተት መስራቱን አምነዋል።
ለሁለተኛ ጊዜ እንደዚህ አይነት ጥፋት እንዳይደገም ማስተካከያ እያደረጉ መሆኑንም ጨምረው ገልጸዋል።
የኦሮሚያው ግጭት በተባባሰበት ሁኔታ የትግራይ ክልል ኮሚኒኬሽን ቢሮ የኦሮሚያ ብሮድካስት ኔትወርክ/ኦ ቢ ኤን/ ዘረኛ ዘገባ እየሰራ ነው ሲል ማስጠንቀቁን ተከትሎ የክልሉ ሚዲያ ቦርድ የሰጠው አስቸኳይ ምላሽና የወሰደው ርምጃ ብዙዎችን ያነጋገረ ሆኗል።