የሐበሻ ሲሚንቶ ፋብሪካ በኦሮሚያ ባለው ግጭት ሳቢያ ማምረት አቆመ

(ኢሳት ዜና–ጥቅምት 20/2010) ከ16ሺ በላይ ባለአክሲዮኖች ያሉበት የሐበሻ ሲሚንቶ ፋብሪካ በኦሮሚያ ባለው ግጭት ሳቢያ ማምረት ማቆሙ ተነገረ።

በተያያዘ ዜና 5 የዳንጎቴ ከባድ የጭነት ተሽከርካሪዎች በእሳት እንደጋዩ ለማወቅ ተችሏል።

የሀበሻ ሲሚንቶ ፋብሪካ ተቃውሞ በሚያሰሙ ወጣቶች ከጥቅምት 14/2010 ጀምሮ በሆለታ ከተማ ተወሮ ምርት እንዲያቆም መገደዱን የአካባቢው ምንጮች አረጋግጠዋል።

የሀበሻ ሲሚንቶ ፋብሪካ ዋና ስራ አስፈጻሚ ኢንጂነር መስፍን አቢ ችግሩን ለመፍታት ከኦሮሚያ ክልላዊ መንግስትና ከአካባቢው ማህበረሰብ ጋር እየተነጋገርን ነው ብለዋል።

በፋብሪካው የ51 በመቶ ድርሻ ያለው የደቡብ አፍሪካው ፒፒሲ ኩባንያ ወኪሎች ፋብሪካው ስራ ማቆሙን ተከትሎ በጉዳዩ ላይ ለመወያየት አዲስ አበባ ገብተዋል።

የሀበሻ ሲሚንቶ ከፍተኛ የስራ አመራር አባላትና ለፋብሪካው ብድር ያቀረቡ የውጭና የሀገር ውስጥ ባንኮች በችግሩ ዙሪያ በጎልደን ቱሊፕ ሆቴል ስብሰባ ማካሄዳቸውም ታውቋል።

ይህ በእንዲህ እንዳለም የዳንጎቴ ሲሚንቶ ፋብሪካ አምስት ከባድ የጭነት ተሽከርካሪዎች በኦሮሚያ ክልል ባለው ግጭት የተነሳ በእሳት መጋየታቸው ተገልጿል።

3ቱ ተሽከርካሪዎች የተቃጠሉት በገብረጉራቻ ከተማ በተፈጠረው ሁከት ነበር።

ሁለቱ ደግሞ ሰሞኑን በአምቦ ከተማ በተካሄደው ተቃውሞ መቃጠላቸው ነው የተነገረው።

በኦሮሚያ ክልል የተነሳውን ተቃውሞ ተከትሎ በአካባቢው ያሉ ኢንቨስተሮችን ስጋት ውስጥ መግባታቸውን ሪፖርተር ጋዜጣ በዘገባው አመልክቷል።